ከሮማንያ ምርጫ ጋር በተያያዘ በቲክቶክ ኩባንያ ላይ ምርመራ ተከፈተ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ቲክቶክ በሮማንያ ምርጫ ወቅት የውጭ ጣልቃ ገብነትን አልተከላከለም በሚል ይፋዊ ምርመራ እንደከፈተበት ተገልጿል።
ኮሚሽኑ እንዳስታወቀው የኩባንያውን ፖሊሲ፣ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው የተከፈለባቸው ማስታወቂያዎች፣ ጥቁምታ የሚሰጠውን የቲክቶክ ስርዓት (አልጎሪዝም) እንዲሁም ለመረጃ ማዛባት ያለውን ተጋላጭነት የተመለከቱ መረጃዎች እንፈትሻለን ብሏል።
የባይተዳንስ ንብረት የሆነው ቲክቶክ ለአውሮፓ ህብረት አስፈላጊውን ሁሉ መረጃዎች በየጊዜው ሲሰጥ እንደነበርና በዓለም ላይ የተካሄዱ ከ150 በላይ ምርጫዎች ወቅት በጥንቃቄ መስራቱን ገልጿል።
ኩባንያው ምንም ዓይነት የማስታወቂያ ክፍያ እንዳልተቀበለ እና ፖሊሲውን የጣሱ፣ ሃሰተኛ እና የጥላቻ ንግግር ይዘቶችን ቀድሞ መከላከሉን አስታውቋል።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በፈረንጆቹ ታህሣሥ 5 ቀን 2024 ለኩባንያው በላከው መልዕክት ከሮማንያ ምርጫ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለይቶ እንዲያስቀምጥ ማዘዙን ብራስልስ ሲግናል የተባለ ድረገፅ አስነብቧል።
የሮማንያ ምርጫ የውጭ አካላት እጃቸውን አስገብተዋል በሚል ውጤቱ በሀገሪቱ ፍርድ ቤት መሰረዙ ይታወሳል።
የህብረቱ ፕሬዚዳንት ኡሩስላ ቫን ድርላይን “ዴሞክራሲያችንን ከማንኛውም የውጭ ጣልቃ ገብነት መጠበቅ ይገባናል፤ በተለይ በምርጫ ወቅት ጣልቃ የገባ አካል መኖሩን በተጠራጠርን ጊዜ በፍጥነትና ጠንከር ብለን ርምጃ መውሰድ አለብን” ብለዋል።
ኮሚሽኑ በቲክቶክ ላይ ምርመራ ሲካሂድ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑን መረጃው ጨምሮ ገልጿል።
ኮሚሽኑ በቅርቡ በሚካሄዱት የጀርመንና የክሮሺያ ምርጫዎች ላይ የውጭ አካላት ጣልቃ ሊገቡ ይችላሉ ብሎ እንደሚያምን አስታውቋል።