Fana: At a Speed of Life!

ሕፃን ልጅ በማገት 4 ሚሊየን ብር የጠየቀው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ ለሚ ከተማ የ11 ዓመት ሕፃን ልጅ በማገት 4 ሚሊየን ብር የጠየቀው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።

 

አበራ አላዩ  የተባለው ግለሰብ ከሚኖርበት ሸገር ከተማ በመነሳት አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ ዎኮ ፍቅረሰላም ቀበሌ ከሚኖር ገብረመድህን አላዩ ከተባለ ወንድሙ ጋር በመሆን ህዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ 4:30 እገታውን መፈፀማቸው ተገልጿል፡፡

 

ድርጊቱንም  በወረዳው ለሚ ከተማ የሚገኘውን አውሌ ገብሩ የተባሉ ግለሰብ መኖሪያ ቤትን ሰብረው በመግባት ጥይት ተኩሰው በማስፈራራት የታጋቹን እናትና እህቶቹን እጅ በገመድ በማሰር ሕፃን ባሳዝነው አውሌን አግተው መውሰዳቸው ተመላክቷል፡፡

 

ሕፃኑንም ለሦስት ቀናት ዋሻ ውስጥ በማሳደርም  ይዘው በእግር እስከ ፍቼ ከተጓዙ በኋላ ሁለተኛው አጋች ገብረመድን አላዩ ወደ አማራ ክልል መመለሱም ተገልጿል፡፡

 

ከዚያም አጋቹ ሕፃኑን ህመምተኛ በማስመሰል በብርድልብስ በመሸፈን በሕዝብ ትራንስፖርት ከፍቼ ከተማ ወደ ሸገር ከተማ ቡራዩ ክ/ከተማ በማድረስ በተከራየው መኖሪያ ቤት ውስጥ በመደበቅ ለሕፃኑ አባት ስልክ በመደወል 4 ሚሊየን ብር እንዲከፍል ጠይቋል ነው የተባለው ።

 

ይህ ካልሆነ ግን ሕፃኑን በሕይወት እንደማያገኘው በማስፈራራት ላይ እንዳለ ጉዳዩን የሰማው አዲስ አበባ ከተማ የሚኖረው የሕፃኑ አጎት ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መረጃውን ማድረሱም ተገልጿል፡፡

 

በዚህም  ፖሊስ መረጃውን  መነሻ በማድረግ  ተጠርጣሪውን ተከታትሎ በተከራየው መኖሪያ ቤት ውስጥ ከተባባሪ ባለቤቱ ጋር እጅ ከፍንጅ በመያዝ በቁጥጥር ስር አውሎ የሕፃኑን ሕይወት መታደግ መቻሉን የፌደራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.