በ88 ዓመታቸው ማራቶን የተወዳደሩት አዛውንት
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) እድሜ እየጨመረ ሲሄድ አቅም እያነ ጉልበት እየከዳ እንኳን ከ42 ኪሎ ሜትር በላይ መሮጥ ይቅርና ከተቀመጡበት ለመነሳት ይከብዳል።
እንደልብ እራስን ችሎ መንቀሳቀስ ፈተና ይሆንና በምርኩዝ ብሎም በሌሎች ሰዎች ድጋፍ መንቀሳቀስ ይመጣል።
የ88 ዓመቱ ፕሉታርቾስ ፖዩርሊያካስ ግን ለዚህ የተፈጥሮ ሕግ እጅ አልሰጡም፤ አዛውንቱ ከ42 ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝመውን ማራቶን በ6 ሰዓት ከ31 ደቂቃ በማጠናቀቅ አነጋጋሪ ሆነዋል።
ለ12 ተከታታይ ጊዜ የአቴንስ ማራቶንን በመሮጥ ያጠናቀቁት እኚህ ጠንካራ አዛውንት፤ በ80ዎቹ መጨረሻ ላይ ላለ ሰው እጅግ የማይሞከር የሚመስለውን የማራቶን ውድድር አዛውንቱ ፕሉታርቾስ አጠናቀው መነጋገሪያ ሆነዋል።
አዛውንቱ በ73 ዓመታቸው ሩጫ የጀመሩት የአልትራ ማራቶን ሯጭ ልጃቸውን በማየት እና የመነሳሳት ስሜት በውስጣቸው በመፈጠሩ እንደሆነ ተነግሯል።
ከዚያም በየቀኑ ከአራት እስከ አምስት ኪሎ ሜትር እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ እስከ 20 ኪሎ ሜትር በመሮጥ ልምምድ አድርገው ወደ ማራቶን መንደር ብቅ ብለው የአቴንስ ማራቶንን 12 ጊዜ በመሮጥ አጠናቀዋል።
ምንም እንኳን እድሜያቸው ቢገፋም ባለፈው ዓመት ካጠናቀቁበት ሰዓት አንጻር ዘንድሮ 18 ደቂቃ ማሻሻል ችለዋል።
አዛውንቱ ማራቶኑን ካጠናቀቁ በኋላ ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ደስታቸውን ገልጸዋል።
“ባለፈው ዓመት ካጠናቀኩበት ሰዓት ዘንድሮ ማሻሻል መቻሌ የ88 ዓመት አዛውንት ሳይሆን ወጣት እንደሆንኩ ይሰማኛል” ሲሉ ተናግረዋል።
የአዛውንቱ ውጤት ሰው ያሻውን ለማድረግ እድሜ እንደማይገድበው እና የፈለገውን ለማሳካት ጥረቱ ብቻ በቂ መሆኑን ያሳያል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።
በኢትዮጵያም ዕድሜያቸው ከ100 ዓመት የተሻገረው የቀድሞ አትሌት ዋሚ ቢራቱ በአትሌቲክስ ውድድሮች በመሳተፍ ብዙዎችን የሚያስደምም ብቃታቸውን እንደሚያሳዩ ይታወቃል።