ሮናልዶ ለፕሬዚዳንትነት እወዳደራለሁ አለ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብራዚል እና ሪያል ማድሪድ የቀድሞ አንጋፋ ተጫዋች ሮናልዶ ሉዊስ ናዛሪዮ ዲሊማ ለብራዚል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነት ልወዳደር ነው ብሏል፡፡
የ48 ዓመቱ የቀድሞ ዝነኛ ተጫዋች የወቅቱን የብራዚል እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኤድናልዶ ሮድሪጌዝ ለመተካት በሚደረገው ምርጫ በዕጩነት እንደሚቀርብ ይፋ አድርጓል፡፡
አምስት ጊዜ የዓለም ዋንጫን በማንሳት ባለክብረወሰኗ ብራዚል ለመጨረሻ ጊዜ ዋንጫውን ከፍ ካደረገችበት በፈረንጆቹ 2002 ወዲህ ከሩብ ፍጻሜ መሻገር ተስኗታል፡፡
በዚህም ብራዚላውያን በተለያየ ችግር ውስጥ እያለፉ እንኳን ብቸኛ መጽናኛቸው እግር ኳስ ነው ያለው ሮናልዶ ÷ አሁን ላይ ዘርፉ እንደሀገር ያለው ውድቀት ሕዝቡን ቅር አሰኝቷል ብሏል፡፡
በመሆኑም የብራዚል ብሔራዊ ቡድንን ወደ ቀድሞ ክብሩ መመለስ እፈልጋለሁ፤ ለዚህም ለፕሬዚዳንታዊ ውድድሩ እንዲረዳኝ በስፔኑ ክለብ ሪያል ቫላዶሊድ ያለኝን ድርሻ ለመሸጥ ወስኛለሁ ነው ያለው፡፡
የወቅቱ ፕሬዚዳንት ሮድሪጌዝ የስልጣን ዘመን በፈረንጆቹ 2026 የሚያበቃ ሲሆን÷ የቀጣዩ ፕሬዚዳንት ምርጫ ከአንድ ዓመት በፊት መጠናቀቅ እንዳለበት ተገልጿል፡፡
ከብራዚል ብሔራዊ ቡድን ጋር በፈረንጆቹ 1994 እና 2002 የዓለም ዋንጫን ያነሳው ሮናልዶ÷ በውድድሩ 15 ግቦችን በማስቆጠር ከጀርመናዊው ሚሮስላቭ ክሎዝ በመቀጠል ሁለተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡