የአንካራው ስምምነት ለቀጣናው ሰላምና ዕድገት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል በወንድማማችነት እና በጋራ መከባበር ላይ ተመስርቶ የተፈረመው የአንካራው ስምምነት ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና እድገት ወሳኝ መሆኑን የአለም አቀፍ ጉዳዮች ተንታኝ፣ የመገናኛ ብዙሃን አማካሪ እና የአፍሪካ ጉዳዮች ጸሃፊ መኪ ኤልሞግራቢ ተናግሯል፡፡
ስምምነቱ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካካል ውጥረትን በማርገብ በትብብር መስራት የሚችሉበትን እድል የፈጠረ መሆኑን ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ ያደረገው መኪ ኤልሞግራቢ አስረድቷል፡፡
የቀጣናው ሀገራት ታሪክ፣ ባህል እና ቋንቋን የሚጋሩ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ በቱርክ አሸማጋይነት ሀገራቱ ስምምነት መፈረማቸው ታሪካዊ ድል መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሰላም እና ጸጥታ ለማጽናት የከፈለችው መስዋዕትነት ከፍተኛ መሆኑን ገልጾ፤ ሶማሊያ በአንካራው ስምምነት ወቅት ለኢትዮጵያ አበርክቶ ዕውቅና መስጠቷ ተገቢ መሆኑን አስገንዝቧል።
ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እና እድገት ቁርጠኝነት እንዳላት የገለጸው መኪ ኤልሞግራቢ፤ የአንካራው ስምምነት የባህር መተላለፊያ ጉዳይ ለኢትዮጵያ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ የተንጸባረቀበት ነው ብሏል፡፡
ሀገራት እና መሪዎች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለቀጠናው ጠቃሚ መሆኑን መረዳት ይኖርባቸዋል በማለት ገልጾ፤ በአረንጓዴ ሃይል ዘርፍ ቀጠናውን ያስተሳሰረችበት መንገድ ለዚህ ተጨባጭ ማሳያ ነው ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣናን ሰላም እና መረጋጋት ለማስፈን እንዲሁም የኢኮኖሚ ውህደትን ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኗን አስታውሶ፤ የአንካራዉ ስምምነት የሀገሪቱን የዲፕሎማሲ እና ኢኮኖሚ ተሳትፎን የሚያሳድግ ነው ብሏል፡፡
የኢትዮጵያን የባህር መተላለፊያ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ማድረግ ለቀጣናው እያደረገች ያለውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ይረዳል ሲል ገልጿል።
መኪ ኤልሞግራቢ በማጠቃለያ ሀሳቡ የአንካራው ስምምነት ኢትዮጵያ የቀጣናው ሰላም እንዲሁም የዲፕሎማቲሲ እና ኢኮኖሚ ትብብሮች እንዲጠናከሩ ቁርጠኛ መሆኗን ያሳየችበት መሆኑን ተናግሯል።
በአቤል ንዋይ እና ወንደሰን አረጋኸኝ