በአፋር ክልል ከቴምር ምርት የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየተሠራ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቴምር ምርታማነትን በማስፋፋት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የአፋር ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የክልሉ መልከዓ-ምድር እና የዓየር ጸባይ ለቴምር ተክል ምቹ ቢሆንም በሚፈለገው ልክ ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን አለመቻሉን በቢሮው የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ የሆርቲካልቸር ልማት ዳይሬክተር አሕመድ አሚን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአፋምቦ እና አሳኢታ ወረዳዎች 302 ነጥብ 5 ሔክታር በቴምር ተክል መሸፈኑን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ 10 ሔክታሩ በአንድ የግል ባለሀብት እየለማ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት 49 ሺህ 741 የቴምር ተክል መኖሩን እና ከአንድ የቴምር ተክል በአማካይ እስከ 30 ኪሎ ግራም ምርት እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
1 ሺህ 753 ከፊል አርብቶ አደሮችም በዘርፉ በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
የቴምር ምርት ፍሬው ለጤና ከሚሰጠው ጥቅም በተጨማሪ ተክሉ በክልሉ ለቤት መስሪያነት (አፋር ዓሪ)፣ ለቤት ውስጥ ምግብ ማቅረቢያ እና ባሕላዊ ቁሳቁሶች፣ ለምንጣፍ ሥራ፣ ለዓየር ማቀዝቀዣ (አፋምቦ ፋን) እንዲሁም ለአፈርና ውኃ ጥበቃ አገልግሎት ይውላል፡፡
ይህን ዘርፈ ብዙ-ጥቅም ያለው ተክል በክልሉ በስፋት ለማምረት እና ዘርፉን ለባለሃብቶች ክፍት በማድረግ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን ነው ያመላከቱት፡፡
በክልሉ ከውጭ የገቡ 14 ዓይነት እና ሁለት ሀገር በቀል የቴምር ዝርያዎች መኖራቸውንም ነው የገለጹት፡፡
በዮሐንስ ደርበው