የአንካራው ስምምነት በዲፕሎማሲ ብዙ ድሎችን ማሳካት እንደሚቻል ያሳየ ነው – ክልሎች
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንካራው ስምምነት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ብዙ ድሎችን ማሳካት እንደሚቻል ያሳየ ነው ሲሉ የአፋር እና ጋምቤላ ክልሎች ገለጹ፡፡
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ÷ኢትዮጵያና ሶማሊያ የደረሱበትን የአንካራ ስምምነት አስመልከተው ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡
አቶ አወል በዚህ ወቅት÷ኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆኗን ተከትሎ ለበርካታ ዓመታት በኪራይ ወደብ ስትጠቀም መቆየቷንና በዚህም ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ማድረጓን አንስተዋል፡፡
በአንካራ የተደረሰው ስምምት ኢትዮጵያ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት አለማቀፉ ማህበረሰብ የተረዳበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ የጋምቤላ ክልል መንግስት ካቢኔ አባላት የአንካራውን ስምምነት አስመልክተው ባደረገው ውይይት ስምምነቱ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ እድገት ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ስምምነቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ሚና ለማሳነስና ለመጋፋት አሉታዊ ሚና ሲጫወቱ የነበሩ አካላት ሁሉ አርፈው እንዲቀመጡ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት ለተደረሰው ስምምነት ለተግባራዊነቱ የክልሉ መንግስት የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
የአንካራው ስምምነት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ብዙ ድሎችን ማሳካት እንደሚቻል አሳይቷል መባሉንም የክልሎቹ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡