Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የመዘመንና የዕድገት ጉዞ በጥራት ላይ የተመሰረተ ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገራችን አምራች እና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በሚፈጠሩ ዓለም አቀፍ የገበያ እድሎች ተወዳዳሪና አሸናፊ እንዲሆኑ የጥራት መስፈርቶችን በሚገባ መገንዘብ እና መተግበር ይገባል ሲሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ አስገነዘቡ።

11ኛው ሀገር አቀፍ የተቋማት የጥራት ሽልማት የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በተገኙበት በታላቁ ቤተ-መንግስት ተካሂዷል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)፣ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ቴዎድሮስ መብራት፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ታድመዋል።

በተለያዩ ዓለም አቀፍ መስፈርቶች ብቁ የሆኑ የምርትና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችም የጥራት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፥ ኢትዮጵያ ለጥራትና ተወዳዳሪነት ትኩረት ሳትሰጥ በመቆየቷ ወደ ኋላ መቅረቷን ገልጸው፥ አዲሱ የኢትዮጵያ የዕድገትና የመዘመን ጉዞ ከዘላቂ ልማትና ከጥራት ጋር የተቆራኘ ነው ብለዋል።

በዚህ ዘመን ጥራት የዓለም የጂኦ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ዋነኛ መወዳደሪያ እየሆነ መምጣቱን መረዳት እንደሚገባ ገልጸው፤ በጥራት ያመረቱና አገልግሎት የሰጡ ሀገራት ወደ ከፍታ ሲደርሱ፥ ትኩረት ያልሰጡት ደግሞ ወደ ኋላ መቅረታቸውን አንስተዋል።

የተጠቃሚና የተገልጋይን የግንዛቤ ክፍተት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዝቅተኛ ጥራት ባለው ምርትና አገልግሎት ገበያውን የሚቀላቀሉ አካላት ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም የሆነው ለጥራት ያለን ባህልና አስተሳሰብ ደካማ በመሆኑ ነው ብለዋል።

መንግሥት ለጥራት በሰጠው ልዩ ትኩረት ኢትዮጵያን ወደ ፊት የሚያራምድ የጥራት መንደር መገንባቱን አንስተዋል።

የጥራት መንደሩ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ሁኔታን በቅጡ የመረዳታችን ዐቢይ ምስክር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፥ ይህ አይነቱ ተቋማዊ ግንባታ ሀገራዊ የጥራት አጀንዳችንን ከፍ ያደርገዋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያን የአፍሪካ የዕድገትና የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አምራቾችና አገልግሎት ሰጪዎች የሀገርን ህልም ለማሳካት፣ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪና አሸናፊ ለመሆን የጥራት መስፈርቶችን መገንዘብና ማሟላት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) በበኩላቸው ተሸላሚዎች በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች መለየታቸውን ገልጸዋል።

የሽልማቱ መሰረታዊ ዓላማ ጥራት ባህል እንዲሆን እና ይህንንም ማስረጽ እንዲቻል መሆኑን አንስተው፤ ጥራት ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና እያደረገችው ላለው ጉዞ አይነተኛ ግብዓት መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.