Fana: At a Speed of Life!

ጤና ሚኒስቴር የከንፈርና ላንቃ ክፍተት ቀዶ ህክምናን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የከንፈርና ላንቃ ክፍተት ቀዶ ህክምና ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ማዕከል በዘመናዊ መሳሪያዎች የተደራጀ የጥርስ ህክምና ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀመሯል።

ማዕከሉ ‘ኦፕሬሽን እስማኤል ኢትዮጵያ’ ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ለአገልግሎት ክፍት መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ስራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር አህመድ ዜኑዲን ገልጸዋል።

ማዕከሉ በዘላቂነት ጥራት ያለው የጥርስ፣ የከንፈርና ላንቃ ህክምናን መስጠት በሚያስችል ዘመናዊ መሳሪያዎች የተደራጀ በመሆኑ የተሟላ ህክምና ለመስጠት እንደሚያስችል የገለጹት ደግሞ የኦፕሬሽን እስማኤል የሰብ ሳሀራን ሪጅናል ዳይሬክተር ዐብይ ሰሙንጉስ ናቸው።

የኦሮሚያ ጤና ቢሮ የስፔሻሊቲ እና የሪሀብሊቴሽን አገልግሎት አስተባባሪ አብዲ ለገሰ ማዕከሉ የከንፈርና የላንቃ ክፍተት ኖሮባቸው ለሚወለዱ ህጻናት እና አዋቂዎች የቀዶ ህክምና ከመስጠት ባለፈ አስፈላጊ የስነ ልሳን ህክምና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስቴር የህክምና አገልግሎት መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ኢሉባቦር ቡኖ በበኩላቸው እንደ ሀገር የከንፈርና ላንቃ ክፍተት ኖርባቸው የሚወለዱ ህጻናትን ማከም የሚያስችል ስትራቴጂ ተቀርጾ እየተሰራበት መሆኑን ገልጸዋል።

የከንፈርና ላንቃ ቀዶ ህክምና የተደረገላቸው ህጻናት ቀጣይነት ያለው የስነ ልሳን እና አስፈላጊ የህክምና እገዛ እንዲያገኙ ለማስቻል ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በወርቃፈራው ያለው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.