የአንካራው ስምምነት እና የቀጣናውን ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎች
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መንግስት መካከል የተደረሰው የአንካራ ስምምነት የቀጣናውን ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎችን ዕኩይ ተልዕኮ ማክሸፉን ምሁራን ገለፁ፡፡
የሀገራቱ መሪዎች አንዳቸው የሌላኛውን ሉዓላዊነት፣ ነጻነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት እና በአፍሪካ ሕብረት ደንቦች ላይ የሰፈሩ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ለማክበር መስማማታቸው ይታወቃል፡፡
የባሕር በር ጥያቄው የኢትዮጵያን ሰላም እና ደኅንነት በማይፈልጉ ኃይሎች በተሳሳተ መልኩ እንዲታይ ለማድረግ ሙከራ መደረጉን የዲፕሎማሲ ባለሙያው ጥላሁን ሊበን ተናግረዋል፡፡
በባሕር በር ጥያቄው ማግስት የሶማሊያ መንግስት አንስቶት የነበረውን ቅሬታ ተከትሎ የቀጣናውን ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎች የሀገራቱን ቅራኔ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ዕኩይ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ጥረዋል ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከትናንት በስቲያ በወዳጅነትና የመከባበር መንፈስ ያለፉ ልዩነቶችን እና አወዛጋቢ ጉዳዮችን ወደ ኋላ በመተው በትብብር ለጋራ ብልጽግና ወደፊት ለመሥራት መስማማታቸው የዕኩይ ኃይሎችን ሴራ አክሽፏል ነው ያሉት፡፡
ይህም የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ትብብር እና የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲቀጥል ከማድረግ በተጨማሪ የቀጣናውን ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎችን ያሳፈረ ስኬታማ ተግባር መሆኑን ነው ያነሱት፡፡
በሉዓላዊ የሶማሊያ መንግሥት ስር ኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ዘላቂ የባሕር መተላላፊ እንድታገኝ የሚያስችል ለሁለቱም ሀገራት ጠቃሚ የሆኑ የኮንትራት፣ የኪራይ እና ተመሳሳይ የንግድ አሠራር መንገዶችን በጋራ በመሆን ለማጠናቀቅ መስማማታቸውንም አንስተዋል፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ደረጀ ፍቅሬ በበኩላቸው÷ የአንካራው ስምምነት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እና ተቋማት ላይ ተቀባይነቷ ከፍ እንዲል አድርጓታል ብለዋል፡፡
በስምምነቱ መሠረት የሶማሊያን የግዛት አንድነት ባከበረ ሁኔታ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር መተላላፊያ ማግኘቷ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ሁለቱ ሀገራት ዕውቅና እንደሚሰጡም ጠቅሰዋል፡፡
ስምምነቱን ተከትሎም ሶማሊያ በአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ ስር ሆነው በሀገሯ የተሰማሩትን የኢትዮጵያ ወታደሮች መስዋዕትነት ዕውቅና እንደምትሰጥ አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም ስምምነቱ የሁለቱ ሀገራትን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ባከበረ መልኩ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ለቀጣናዊ ትስስር እና የጋራ እድገት እሳቤ ጠንካራ አቋም ያለው ሲሆን÷ መንግስት ባለፉት ስድስት ዓመታት ይህንን የወንድማማችነት እሳቤ የሚያረጋግጡ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል ብለዋል፡፡
ለአንካራው ስምምነት መደረስም መንግስት ለቀጣናዊ ትብብር ያለውን ቁርጠኛ አቋም የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው÷ ይህ የወንድማማችነት እሳቤ የኢትዮጵያ መንግስት በዓለም አቀፍ ተቋማት ውዳሴ አስገኝቶለታል ነው ያሉት፡፡
በሚኪያስ አየለ