በጽ/ቤቱ እየተገነባ የሚገኘው ት/ቤቱ የአርብቶ አደር ልጆች ትምህርታቸውን በቅርበት እንዲከታተሉ የሚረዳ ነው – ነጋሽ ዋጌሾ (ኢ/ር፣ ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽ/ቤት ድጋፍ በምዕራብ ኦሞ ዞን እየተገነባ የሚገኘው ትምህርት ቤት የአርብቶ አደር ልጆች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚረዳ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ኢ/ር፣ ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽህፈት ቤት እየተገነባ ያለውን የቱልጊት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ጎብኝተዋል፡፡
የትምህርትቤቱ ግንባታ አፈጻጸም በተያዘለት ጊዜ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽህፈት ቤት በጀት ድጋፍ በምዕራብ ኦሞ ዞን ሱሪ ወረዳ ቱልጊት ቀበሌ እየተገነባ የሚገኘው የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአርብቶ አደሩ ልጆች በቅርበት ሆነው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚረዳ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ግንባታው ያለበት ደረጃ የሚበረታታ መሆኑንና በተያዘለት ጊዜ ተጠናቅቆ የመማር ማስተማር ስራውን እንዲጀምር ርዕሰ መስተዳድሩ አቅጣጫ መስጠታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡