በመዲናዋ በኮሪደር ልማት ሥራ የትራፊክ አደጋዎችን መቀነስ መቻሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በተሰራው የኮሪደር ልማት ሥራ ባለፉት አምስት ወራት የትራፊክ አደጋዎችን መቀነስ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሪደር መሰረት ልማት ጥምር ግብረ ኃይል የአምስት ወራት የኮሪደር መሰረት ልማት እቅድ አፈፃፀም ስራዎችን ገምግሟል።
በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ክበበው ሚደቅሳ በኮሪደር ልማት ስራ ለትራፊክ ፍሰት ምቹ ያልሆኑ መንገዶች እንዲስተካከሉ በመደረጋቸው የትራፊክ አደጋዎችን መቀነስ እንደተቻለ መግለጻቸውን ከከተማው ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ በበኩላቸው ፥ አዲስ አበባን ውብ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ በኮሪደር ልማቱ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ባለፉት አምስት ወራት ጥምር ግብረ ኃይሉ በቅንጅት በሰራው ስራ 266 ድርጅቶች እና 19 ሺህ በሚሆኑ ግለሰቦች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ ከ103 ሚሊየን ብር በላይ የማስተማሪያ ቅጣት በመቅጣት ወደ መንግስት ካዝና ገቢ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡