በኢትዮጵያ የክልል የኢኮኖሚ አካውንት መመሪያ ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)የፕላንና ልማት ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የክልል የኢኮኖሚ አካውንት መመሪያን ይፋ አድርጓል።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ፕላንና ልማት ቢሮ ሃላፊዎች በተገኙበት በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የክልል ኢኮኖሚ አካውንት የአሰራር ዘዴ መመሪያ በቢሾፍቱ በተካሄደ መድረክ ይፋ አድርጓል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ፍስሀፂዮን እንደገለፁት ፥ የክልል የኢኮኖሚ አካውንት የክልሎችን ኢኮኖሚያዊ አፈጻጸም ለመለካት የሚያገለግል መሳሪያ ነው።
ኢትዮጵያ በ1953 ዓ/ም ብሔራዊ የኢኮኖሚ አካውንት ተግባራዊ ማድረግ የጀመረች ቢሆንም እስከአሁን ድረስ የክልል የኢኮኖሚ አካውንት እንዳልነበራት ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሮችና ክልሎች ከዚህ ቀደም የኢኮኖሚ ሁኔታቸውን ለመለካት ወጥ ያልሆነ እና ከብሔራዊ የኢኮኖሚ አካውንት ጋር ያልተናበበ ስርዓትን ይከተሉ እንደነበር ገልጸው ፥ ይህም በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎችን ለመወሰን አዳጋች አድርጎት መቆየቱን ጠቅሰዋል።
ፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከዚህ በመነሳት ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የክልል የኢኮኖሚ አካውንት የአሰራር ዘዴ መመሪያን ሲያዘጋጅ መቆየቱን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው ፥ መመሪያው በአሁኑ ወቅት ተጠናቅቆ ይፋ ተደርጓል ብለዋል፡፡
የክልል የኢኮኖሚ አካውንት መመሪያው የክልሎችን የኢኮኖሚ ባህሪ ለመከታተልና እርምጃዎችን ለመውሰድ ትክክለኛ የመረጃ ምንጭ ሆኖ እንደሚያገለግልም ነው ያብራሩት።
መመሪያው ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መዘጋጀቱን ጠቁመው ፥ ፖሊሲዎችን ለማውጣትና ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎችን ለመወሰን የሚያስችል የመረጃ ምንጭ እንደሚሆን መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።