ንግድ ባንክና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የክፍያ አሰባሰብን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶችን የክፍያ አሰባሰብ ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡
ስምምነቱ 26 የሚሆኑ የፌዴራል የመንግስት መሥሪያ ቤቶች እና በስራቸው የሚገኙ 360 ተቋማት ለተገልገዮች የሚሰጧቸው አገልግሎቶችን ክፍያ በዲጂታል አማራጭ የሚቀበሉበትን መንገድ ያመቻቸ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት የባንኩ የዲጅታል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ወጋየሁ ገ/ማሪያም ÷ ስምምነቱ ተቋማቱ ክፍያቸውን በሲቢኢ ብር አማካኝነት ለመሰብሰብ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዲጂታል ክፍያ አማራጩ ለአጠቃቀም ምቹ እንዲሁም ጊዜና ጉልበትን የሚቆጥብ በመሆኑ ህብረተሰቡ በስፋት እንዲጠቀምበት ጠይቀዋል፡፡
ባንኩ ቀደም ሲልም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያስችል ተመሳሳይ የሥራ አጋርነት ከሌሎች ተቋማት ጋርም ፈጥሯል መባሉን የንግድ ባንክ መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ የሺሁን አለማየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ ስምምነቱ የመንግስትን አሠራር ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ አይነተኛ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ 80 በመቶ የሚሆነውን የመንግስት የክፍያ ስርዓት ዲጂታላይዝ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ይህም ግልፀኝነትን፣ ፍትሀዊነትንና ቀልጣፋ አሠራርን በማስፈን ለመልካም አስተዳደር መጎልበት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው አብራርተዋል፡፡