የአገልግሎቱን ሪፎርሞች ውጤታማ ለማድረግ የመንግስት ትኩረት ተጠናክሮ ይቀጥላል – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሪፎርሞች ውጤታማ ለማድረግ የመንግስት ትኩረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷ ዛሬ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በደንበኛ አገልግሎት መስጫ እና በጥሪ ማዕከል የመስክ ምልከታ በማድረግ ተቋሙ ለደንበኞቹ የሚሰጠውን አገልግሎት የተሻለ ለማድረግ እያከወናቸው የሚገኙ የሪፎርም ሥራዎችን መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡
አገልግሎቱ በርካታ ደንበኞችን የማስተናገድ አቅሙን በማሳደግ እንግልትን ለመቀነስና ግልጽ የአሠራር ሥርዓትን ለመተግበር ባከናወናቸው ተግባራት ላይ ተወያይተናል ብለዋል፡፡
በደንበኛ አገልግሎት መስጫ፣ በዳታ ሴንተር እና በጥሪ ማዕከል እየተተገበሩ በሚገኙ ሥራዎች የኤሌክትሪክ ኃይልን በማቅረብ ተልዕኮ ሂደት የሚያጋጥሙ መሠረታዊ ተግዳሮቶችን በዘላቂነት ለመፍታት በሚያስችሉ ተግባራት ላይም አቅጣጫ አስቀምጠናል ነው ያሉት፡፡
የተቋሙን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ተገቢ እና ጠቃሚ ሪፎርሞችን በትኩረት እና ትጋት በመፈፀም ውጤታማ መሆን የመንግስት ትኩረት በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አስገንዝበዋል።