በሻምፒየንስ ሊጉ አተላንታ ከሪያል ማድሪድ የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የምድብ ስድስተኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ሲካሄዱ ቤርጋሞ ላይ አተላንታ ሪያል ማድሪድ እና አተላንታ የሚያደርጉት ፍልሚያ በጉጉት ይጠበቃል፡፡
ምሽት 2 ሠዓት ከ45 ላይ ዳይናሞ ዛግሬብ ከሴልቲክ እንዲሁም ዢሮና ከሊቨርፑል ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
በሌላ የጨዋታ መርሐ-ግብር ምሽት 5 ሠዓት ጌዊስ ስቴዲየም ላይ አተላንታ ከሪያል ማድሪድ የሚያደርጉት ግጥሚያ የምሽቱ ተጠባቂ ጨዋታ ነው፡፡
አተላንታ እስከ አሁን ባደረጋቸው አምስት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ግጥሚያዎች ሦስቱን በማሸነፍ እና ሁለቱን አቻ ሲለያይ÷ ሪያል ማድሪድ ሁለት ጨዋታዎችን አሸንፎ በሦስቱ መሸነፉ ይታወሳል፡፡
መሸነፍ ከውድድሩ በቀጥታ የሚያሰናብተው ሪያል ማድሪድ÷ ማሸነፍን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡
በዘንድሮው የውድድር ዓመት በአውሮፓ መድረክ ያለመሸነፍ ጉዞውን ያስቀጠለው አተላንታ÷ የጣሊያን ሰሪኤውንም በአንደኝነት እየመራ መሆኑ ጨዋታውን በይበልጥ አጓጊ አድርጎታል፡፡
ሎስብላንኮሶቹ በጨዋታው የሚሸነፉ ከሆነ በታሪክ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ባነሳ በአመቱ በውድድሩ የምድብ ሶስት ጨዋታዎችን በተከታታይ የተሸነፈ ብቸኛው ክለብ በመሆን አስከፊ ታሪክ ያጽፋል፡፡
ሪያል ማድሪድ ከጉዳት የተመለሱትን ብራዚላዊያን ቪኒሽየስ ጁኒየር እና ሮድሪጎን አገልግሎት ያገኛል፡፡
በተመሳሳይ ምሽት 5 ሠዓት ላይ ባየርሊቨርኩሰን ከኢንተርሚላን፣ ብረስት ከፒኤስቪ፣ ክለብ ብሩጅ ከስፖርቲንግ ሊዝበን፣ አርቢ ሌብዢግ ከአስቶንቪላ፣ ሬድቡል ሳልዝበርግ ከፒኤስጂ እንዲሁም ሻክታር ዶኔስክ ከባየርንሙኒክ ይፋለማሉ፡፡