ዘር ማጥፋት ላይ ያተኮረ የጥላቻ ንግግርን ለመግታት የጋራ ጥረት እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዘር ማጥፋት ላይ ያተኮረ የጥላቻ ንግግርን ለመግታት የጋራ ጥረት እንዲደረግ የአፍሪካ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ አዳማ ዴንግ ጥሪ አቀረቡ፡፡
በኪጋሊ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የዘር ማጥፋት መከላከል ጉባዔ ላይ የተሳተፉት አዳማ ዴንግ÷ በፈረንጆቹ 1994 በርዋንዳ ቱትሲ ላይ የተፈፀመውና 1ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች የተገደሉበት የዘር ማጥፋት ዘመቻን አስታውሰዋል፡፡
በመሆኑም ዘረኝነትን እና ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃትን ጨምሮ የሌላ ሀገር ዜጎችን መጥላት እንዲሁም ሁሉንም ዓይነት አለመቻቻሎችን ለመዋጋት የተቀናጀ አስቸኳይ ርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የጥላቻ ንግግር በራሱ መቻቻልን፣ መደመርን፣ ብዝኃነትን፣ የሰብዓዊ መብት ደንቦችንና መርሆዎችን መጣስ ነው ሲሉ በአጽንኦት መግለጻቸውን ዥንዋ ዘግቧል፡፡
ጉባዔው የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከልና ቅጣት ስምምነት 76ኛ ዓመት መታሰቢያ አካል መሆኑን ያመላከተው ዘገባው÷ በፈረንጆቹ 1948 ተቀባይነት ያገኘው ይህ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደዓለም አቀፍ ወንጀል የሚታይ መሆኑን ጠቅሷል፡፡