የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የቡና ንግድ ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የቡና ንግድ ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡
የቻይና አፍሪካ የኢኮኖሚ እና የንግድ ትስስር መማክርት ልዑካን ከኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን እንዲሁም ከቡና ላኪ ድርጅቶች ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት የቻይናው ልዑክ ÷የመማክርቱ ዓላማ በቻይና እና በአህጉሪቱ ሀገራት የሚደረገውን የንግድ ግንኙነት ማሳለጥ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ በቡና ንግድ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው መናገራቸውን ከኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ቡና መግዛት ብቻ ሳይሆን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነትም ማጠናከርና መተጋገዝን ያማከለ ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል።
በዚህም የቻይና ኩባንያዎች በመጪው የፈረንጆች ዓመት 4ኛ ደረጃ ቡና ከ100 ሺህ እስከ 150 ሺህ ቶን ቡና የመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው ተገልጿል፡፡
ባለፈው አመት ቻይና 12 ሺህ 163 ሜትሪክ ቶን የኢትዮጵያ ቡናን እንደገዛች ተመላክቷል፡፡