ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ ሊቀንሱ እንደሚችሉ አመለከቱ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ሲረከቡ ሀገራቸው ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ ሊቀንሱ እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡
ትናንት ምሽት ከኤንቢሲ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ቆይታ ያደረጉት ትራምፕ÷ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት በተመለሱበት ማግስት በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ግፊት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡
ወደ ሃላፊነት ሲመጡ አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ ሊቀንሱ እንደሚችሉ የገለፁት ፕሬዚዳንቱ÷ ውሳኔው የሁለቱ ሀገራት ጦርነት እንዳይባባስ ለማድረግ እንደሚያስችልም አብራርተዋል።
የፔንታጎንን መረጃ ጠቅሶ አርቲ እንደዘገበው፤ ጦርነቱ ከጀመረበት የፈረንጆቹ 2022 አንስቶ እስካሁን አሜሪካ ለዩክሬን 131 ነጥብ 36 ቢሊየን ዶላር በአይነት እና በገንዘብ ድጋፍ አድርጋለች፡፡
ከዚህ ውስጥ 90 ቢሊየን ዶላር በቀጥታ ለዩክሬን የተላለፈ ገንዘብ መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡
በተያያዘ ባላፈው ቅዳሜ ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ጋር የተወያዩት ትራምፕ፤ ዘለንስኪ በሀገራቸው እና በሩሲያ መካከል የተኩስ አቁም እና የሰላም ስምምነት እንዲደረስ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡