በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ከመምጣቱ ባሻገር በፀና የታመሙት ቁጥር ተበራክቷል – ዶ/ር ሊያ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ከመምጣቱ ባሻገር በፀና የታመሙት መበራከት አሳሳቢ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።
በኢትዮጵያ መጋቢት 4 ላይ በ48 አመት ጃፓናዊ ጎልማሳ አንድ ብሎ የጀመረው የኮሮና ቫይረስ በትናንትናው ዕለት 10 ሺህን ተሻግሯል።
ለ331 ሺህ 266 ሰዎች ምርመራ ተደርጎ 10 ሺህ 207 ሰዎች ላይ ቫይረሱ የተገኘ ሲሆን፤ እንደ ሌሎች ሀገራት ከተማ እና እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ሳይዘጋ የመከላከል ስራው ላይ ትኩረት መደረጉ ይታወቃል።
ሰፊ የግንዛቤ የመፍጠር ስራ በማከናወንም ህብረተሰቡ የመከላከያ እርምጃዎችን ሲተገብር ቆይቷል ሆኖም ከቀን ወደ ቀን መሰላቸቱ እና ቫይረሱን አቅልሎ የማየት አዝማሚያ በማህበረሰቡ ዘንድ ተስተውሏል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ ህብረተሰቡ በወረርሽኙ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ቢኖረውም የመከላከያ ዘዴዎቹን መተግበር ላይ ወደኋላ እያለ መሆኑን አንስተዋል።
አሁን ላይ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ከመምጣቱ ባሻገር በፀና የታመሙት መበራከትም አሳሳቢ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ባደረገው ቅኝት፤ በትራንስፖርት ፣ በመዝናኛ ቦታዎች እና ህዝብ በሚበዛባቸው የአገልግሎት መስጫ ስፍራዎች ኮቪድ 19 የሌለ ይመስል የጥንቃቄ እርምጃዎቹ እየተዘነጉ ነው።
የመዲናዋ ነዋሪዎችም ቫይረሱን ለመቆጣጠር የተላለፉ ውሳኔዎች አተገባበር አሁን ላይ እየታየ ካለው የቫይረሱ ግስጋሴ አንፃር ሲመዘን የከፋ ዋጋ እንዳያስከፍለን ያሰጋል ይላሉ።
በአዲስ አበባ ሰብሰብ ብሎ መዝናናት እና የእግር ኳስ ጨዋታዎችን መመልከት ወደ ወትሮው ድባቡ እየተመለሰ ነው።
በተለይም በወጣቶች ዘንድ ትዕግስት የማጣት ነገር እንደሚታይ እና ይህ ሃላፊነት የጎደለው አካሄድም የቫይረሱን ስርጭት ሊያስፋፋ ስለሚችል ሊቆም ይገባዋል ብለዋል የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ያሰማራቸው ከ18 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞችም ከ35 ሚሊየን በላይ ለሚሆን የህብረተሰብ ክፍል የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ መስራታቸውንም ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ወረርሽኙን በመከላከል ስራ ላይ ለተሰማሩ ግለሰቦች እና ተቋማት ምስጋናውን እንደሚያቀርብም ነው የተናገሩት።
መጭው ጊዜ የከፋ እንዳይሆን መታጠብ፣ አፍና አፍንጫን መሸፈን፣ መራራቅ፣ በቤት ውስጥ መቆየት እና መተሳሰብን ጨምሮ በአንድነት በመስራት የቫይረሱን ስርጭት መግታት የሁሉም ዜጋ ወሳኝ ሃላፊነት ነው በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በፋሲካው ታደሰ