የሌላ አካል ይዞታን በሀሰተኛ ሰነድ በ700 ሚሊየን ብር ለመሸጥ የተደራደረው አትሌት በ3 ዓመት ከ4 ወር እስራት ተቀጣ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሌላ አካል ይዞታን በሀሰተኛ ሰነድ በ700 ሚሊየን ብር ለመሸጥ በመደራደር የተከሰሰው አትሌት ድሪባ መርጋ በ3 ዓመት ከ4 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ወሰነ።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ 1ኛ አትሌት ድሪባ መርጋ እና 2ኛ በግል ስራ የሚተዳደሩት ወ/ሮ መንበረ አበበ ገብረጻዲቅ ላይ የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ ተደራራቢ ክሶችን አቅርቦባቸዋል።
በዚህም በ1ኛ ተከሳሽ ላይ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ክስ ቀርቦበታል።
ተከሳሹ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የናይስ ሪል ስቴት ኃ/የተ/የግ/ማህበር የሆነውንና በቂርቆስ ክ/ከ ወረዳ 08 ስር የሚገኘውን 4 ሺህ 972 ካሬ ሜትር ይዞታን በመጋቢት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ከሚመለከተው ተቋም እንደተሰጠ በማስመሰል ተመሳስሎ የተሰራ ሀሰተኛ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ለሶስተኛ ወገን ለሽያጭ ማቅረቡን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ በክሱ አስፍሯል።
በተጨማሪም ተከሳሹ በውል ቁጥር 2036/2012 ዓ.ም ደግሞ በውል ሰጭ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ መሬት ዝግጅትና ማስተላለፍ ዘርፍ እና በውል ተቀባይ ናይስ ሪል ስቴት ኃ/የተ/የግ/ማህበር መካከል የተፈረ በማስመሰል የተዘጋጀ ሀሰተኛ የሊዝ ውል፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የተሰጠ በጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም በኮድ ቁጥር 2929/2929/2015 የሊዝ ውልን በማሻሻል እንደላከ በማስመሰል የተጋጀ ሀሰተኛ የሊዝ ውል ለሽያጭ አቅርቧል።
በተጨማሪም ተከሳሹ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ውክልና ባልሰጠችበት ሁኔታ ላይ በህዳር 5 ቀን 2016 ዓ.ም ለ1ኛ ተከሳሽ ይዞታውን በሽያጭ እስከ ማስተላለፍ ድረስ እንዲያስተዳድር ውክልና እንደሰጠች ተደርጎ የተዘጋጀ ሀሰተኛ ሰነድ ማቅረቡ በክሱ ላይ ተመላክቷል።
1ኛ ተከሳሽ በታህሳስ 4 ቀን 2016 ዓ.ም በይዞታው ላይ የተጠቀሱ ሀሰተኛ ሰነዶችን በማቅረብ ይዞታውን በ700 ሚሊየን ብር ለመሸጥ ሲደራደር የመያዙን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ በሀሰተኛ ሰነድ መገልገል የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦበታል።
ሁለተኛ ክስ ላይ ደግሞ ከዚህ በፊት እስኪያዝ ድረስ ለጊዜው ክሱ በተቋረጠለት ማለትም ስዩም አሰፋ ወንድማገኝ በተባለ ግለሰብ ላይ የቀረበ ክስ ነበር።
ይኸውም ክስ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) ስር የተመለከተውን ተላልፈዋል የሚል ነው።
በዚህም 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለራሳቸው ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት አስበው በ1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር በሆነው እና በስራ አስኪያጅነት የሚተዳደረው ናይስ ሪል ስቴት ኃ/የተ/የግ/ማህበር ይዞታ ላይ ተመሳስሎ የተሰራ ሀሰተኛ ካርታ፣ የሊዝ ውልና የውክልና ሰነድ ማዘጋጀት የሙስና ወንጀል ቀርቦባቸዋል።
3ኛ ክስ ደግሞ በሁለተኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 390 ንዑስ ቁጥር 1 ስር የተመለከተውን መተላለፍ የሚል ክስ ቀርቦባታል።
በዚህም በታህሳስ 4 ቀን 2016 ዓ.ም በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ልዩ ቦታው አረንጓዴ ሰፈር ተብሎ ከሚታወቀው ቦታ አካባቢ በሚገኘው የስራ ቦታዋ ውስጥ በፍርድ ቤት ትእዛዝ መሰረት በተደረገ ብርበራ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በልደታ ክ/ከ ትምህርትና ስልጠና ጽ/ቤት የዕውቀት ለህብረት የ2ኛ ደረጃ ት/ቤት የተማሪዎች ካርድ እና በትምህርት ሚኒስቴር አባይ የመጀመርያ ደረጃ ት/ቤት የተማሪ ውጤት መግለጫ ካርድ የተገኘባት በመሆኑ የሐሰት ስራ ለመፈጸም የሚያገለግሉ መሳርያዎችና መስርያዎች ይዞ መገኘት ወንጀል ተከሳለች።
በዚህ መልኩ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የቀረበባቸው ክስ ዝርዝር በችሎት እንዲደርሳቸው የተደረገ እና ክሱን በንባብ እንዲሰሙ ተደርጓል።
3ኛ ተከሳሽ የተከሰሰበት ድንጋጌ ንዑስ ቁጥር 1 በሌለበት ሊታይ የማይችል በመሆኑ ምክንያት እስኪያዝ ድረስ ለጊዜው ክሱ እዲቋረጥ ተደርጓል።
ከዚህም በኋላ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የእምነት ክህደት ቃል በመስጠታቸው ዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ በተከሰሱበት ድንጋጌ ስር እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ሲሆን ተከሳሾቹ ግን የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መከላከል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።
ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ 1ኛ ተከሳሽ አትሌት ድሪባ መርጋን በ3 ዓመት ከ4 ወራት ጽኑ እስራት እና በ5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።
ሁለተኛ ተከሳሽን በሚመለከት የጤና እክል እንዳለባት፣ ቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኗንና ሌሎች ያቀረበችውን የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ በ2 ዓመት ከ9 ወራት ጽኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንድትቀጣ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ በሁለተኛ ተከሳሽ ላይ የተጣለው ቅጣት እንዲገደብ አድርጓል።
በታሪክ አዱኛ