Fana: At a Speed of Life!

የቦሌ ክፍለከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር የይዞታ ማስተካከል ቡድን መሪ ጉቦ በመቀበል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቅንጫፍ ጽህፈት ቤት የይዞታ ማስተካከል ቡድን መሪ መረጃ በማጉደል እና ጉቦ በመጠየቅ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የፌደራል ፖሊስ ገለፀ፡፡

አሸብር አበባው የተባለው ግለሰብ መረጃ በማጉደል፣ሥልጣንን ያለአግባብ በመገልገል እና ጉቦ በመቀበል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገልጿል፡፡

ተጠርጣሪው የወ/ሮ ሙሉ ካህሺን ሕጋዊ ወኪል የሆኑት አቶ ደራራ ዲንሳ ኢረና በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 የሚገኝ የቦታ ይዞታቸው በመሬት ይዞታ ምዝገባ ኤጀንሲ እንዲረጋገጥላቸው ለቅንጫፍ ጽህፈት ቤቱ አመልክተው፤ተጠርጣሪው የማይገባ ጥቅም በመፈለግ ከአመልካች ማኅደር ላይ መረጃ በማጉደል እና ጉዳያቸውን በማጓተት ሲያጉላላቸው ከቆየ በኋላ መረጃውን አሟልቶ ወደሚመለከተው አካል ለመላክ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ጉቦ መጠየቁን የምርመራ ቡድን ደርሶበታል፡፡

ባለጉዳዩ የተጠቁትን ገንዘብ ወደ ተጠርጣሪው የባንክ ሂሳብ ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ያስገቡ መሆናቸውን ሕዳር 18 ቀን 2017 ዓ.ም ለምርመራ ቡድኑ ጥቆማ አቅርበው ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር ሊውል መቻሉን የፌራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡

የምርመራ ቡድኑ የተጠርጣሪውን የእምነት ክህደት ቃል በመቀበል፣ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆ የ10 ቀን የምርመራ ማጣሪያ እስከ ሕዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት መፍቀዱ ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.