በምክር ቤት ያለመከሰስ መብቱ የተነሳው ሰዒድ አሊን ጨምሮ 8 ግለሰቦች ላይ የሙስና ወንጀል ክስ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ምክር ቤት ያለመከሰስ መብቱ የተነሳው የልደታ ክ/ከተማ የቀድሞ ዋና ስራ አፈጸሚ አቶ ሰዒድ አሊን ጨምሮ ስምንት ግለሰቦች በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የሙስና ወንጀል ክስ ቀረበባቸው።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ በተከሳሾቹ ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1(ሀ)፣ አንቀጽ 33 እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ)፣(ለ) እና ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል እና በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ በሚል ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸዋል።
ክሱ የቀረበባቸው 1ኛ የልደታ ክ/ከተማ የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰይድ አሊ፣ 2ኛ በክ/ከተማው ወረዳ 04 ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የሥራ እና ክህሎት ጽ/ቤት ኃላፊ ደበላ ዳባ፣ 3ኛ በክ/ከተማው ወረዳ 04 መንግስት ቤቶች ጽ/ቤት ኃላፊ አንድነት አብዩ፣4ኛ የመሬት ልማትና አስተዳዳር ጽ/ቤት ተወካይ ሃላፊ ቴዎድሮስ ፀጋዬ፣ 5ኛ በንግድ ስራ የሚተዳደረው ሀጂ በገን ኸይሩን ጨምሮ አምስት የመንግስት ሰራተኞች እና ሶስት በግል ስራ የሚተዳደሩ በአጠቃላይ ስምንት ግለሰቦች ናቸው።
በዚህም 1ኛ ክስ በ1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን፤ ከ1ኛ እስከ 4ኛ የተጠቀሱት ተከሳሾች እንደቅደም ተከተላቸው ኃላፊ ሆነዉ ሲሰሩ በግል ስራ ከሚተዳደረው ከ5ኛ ተከሳሽ ጋር መመሳጠር የሚል ይገኝበታል።
በተለይም ከጥር 29 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በክ/ከተማው ውስጥ ከሜክሲኮ እስከ ቄራ ባለው ዋና መንገድ ማስፋፊያ የኮሪደር ልማት ጥናት መሰረት የሚሰራውን ፕሮጀክት ሽፋን በማድረግ በክፍለ ከተማው ወረዳ 04 ሳልቫቶሬ ዴቪታ ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ ግለሰቦች ተከራይተው የሚገኙትን የቀበሌ ቤቶችን አፍርሰው ይዞታውን የ5ኛ ተከሳሽ ንብረት ለሆነው ዋይልድ አፓርትመንት ለተባለ ህንፃ መጠቀሚያ እንዲሆን ማመቻቸት የሚል በክሱ ይገኝበታል።
በዚህም ከኮሪደር ልማት መስመር ውጪ የሚገኙ ስድስት የመኖሪያ ቤቶች በውስጣቸዉ ግለሰቦች እየኖሩበት እና ንግድ እየተከናወነበት እያለና የከተማዉ ካቢኔ ቤቶቹ እንዲፈርሱ ባልወሰነበት፤ እንዲሁም ፕላን ፎርማት እና የካቢኔ ውሳኔ ባልተያያዘበት ሁኔታ 1ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ቤቶቹ በፍጥነት እንዲፈርሱ ለወረዳ አመራር ለሆኑት 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾችና ለሌሎችም ያለ አግባብ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ በክሱ አስፍሯል።
2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ደግሞ ህገ-ወጥ ትዕዛዝ በመቀበል ቤቶቹ እንዲፈርሱ በቃለ ጉባኤ በመወያየት በሁለት ቀን ውስጥ ቤቶቹን ለማፍረስ የሚያስፈልገዉን የማፍረሻ ግምት በተመለከተም ለ4ኛ ተከሳሽ የማፍረሻ ግምት በሚል በግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ደብዳቤ ጽፎ በመስጠት ቤቶቹ እንዲፈርሱ በማድረግ እንዲሁም በቤቶቹ ነዋሪ ለሆኑ ተነሺዎችም ያለአግባብ በተለያዩ ሳይቶች ምትክ ቤቶች እንዲያገኙ አድርገዋል የሚል ይገኝበታል።
መፍረስ የሌለባቸውን 6 የመኖሪያ እና አንድ የንግድ ቤት በማፍረስ የመንግስት ቤቶቹ ውስጥ በኪራይ ይኖሩ ለነበሩት ግለሰቦች አጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 3 ሚሊየን 383 ሺህ 202 ብር ከ77 ሳንቲም 6 የጋራ መኖሪያ ቤት ኮንዶሚኒየም እንዲሰጣቸው በማድረግ የሚል በክሱ ተካቷል።
እንዲሁም ቤቶቹ የፈረሱበት የቦታ ስፋቱ 503 ካሬ ሜትር ቦታ በህገ ወጥ መልኩ ለ5ኛ ተከሳሽ ንብረት ለሆነ ህንፃ አገልግሎት እንዲውል ለማድረግ 1ኛ ተከሳሽ በአካል ቦታዉ ለይ በመገኘት “ተፈቅዶለታል እንዳትከለክሉት ያልማ” በሚል በቃል ለሁለት የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ለሆኑ ባለሙያዎች ትዕዛዝ መስጠቱ በክሱ ተጠቅሷል።
1ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ሊፈርሱ ማይገባቸዉ የመንግስት ቤቶች ያለአግባብ እንዲፈርሱ ትዕዛዝ በመስጠትና 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ደግሞ ይህንን ህገ-ወጥ ትዕዛዝ ተቀብለው ቤቶችን በማስፈረስ እና ለ5ኛ ተከሳሽ ምቹ በማድረግ ህገ-ወጥ ግንባታ እንዲገነባ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ በመፍቀድ፣ 5ኛ ተከሳሽም በዚሁ ይዞታ ላይ ወይም ቤቶቹ በፈረሱበት ቦታ ላይ ያለአግባብ ህገ-ወጥ ግንባታ እና ማስፋፊያ ስራ መስራቱ በክስ ዝርዝር ላይ ተመላክቷል።
በተለይም ለተነሺዎች ያለአግባብ የመንግስት ጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) እንዲሰጣቸዉ በማድረግ፤ ተከራዮች ያለአግባብ ቤታቸው እንዲፈርስ በማድረግ በመንግስት ላይም የሊዝ ዋጋን ጨምሮ ብር 4 ሚሊየን 362 ሺህ 986ብር ከ89 የሚገመት ጉዳት ያደረሱ መሆናቸዉ በክሱ የጠቀሰው ዐቃቤ ሕግ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተራ ቁጥር የተገለፁት ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት እንዲሁም 5ኛ ተከሳሽ በልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡
በ2ኛ ክስ ደግሞ በ1ኛ፣ 5ኛ፣ 6ኛ፣ 7ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች ላይ 1ኛ ክስ በተጠቀሰው መልኩ 6 ሚሊየን ብር ምንጩ እንዳይታወቅ እንዲሁም ወንጀል ፈፃሚው ከህግ ተጠያቂነት እንዲያመልጥ ለማድረግ ገንዘቡን በባንክ ሂሳባቸው ያስቀመጡ እንዲሁም ያስተላለፉ መሆናቸው ተጠቅሶ ሁሉም ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈፀሙት በወንጀል የተገኘ ንብረት ወይም ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከሰዋል።
ክሱ ለተከሳሾች የደረሰ ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ በክሱ ላይ የክስ መቃወሚያ ካለው ለመጠባበቅ ለህዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም ተቀጥሯል።
በታሪክ አዱኛ