በታዳጊ ማህሌት ተክላይ ላይ የግድያ ወንጀል የፈፀሙ ተከሳሾች ላይ እስከ ሞት የሚደርስ የፍርድ ውሳኔ ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ 23 ሕዳር፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል የመቐለ ከተማ መካከለኛ ፍርድ ቤት በታዳጊ ማህሌት ተክላይ ላይ የግድያ ወንጀል የፈፀሙ ተከሳሾች ላይ የፍርድ ውሣኔ ሰጥቷል፡፡
የ16 ዓመት ታዳጊዋ የዓድዋ ከተማ ነዋሪ ማህሌት ተክላይ መጋቢት 10 ቀን 2016ዓ.ም ወደ ትምህርት ቤት እየሄደች ከነበረበት ታግታ ተወስዳ ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም ተገድላ መገኘቷ ይታወሳል፡፡
አንደኛ ተከሳሽ አንገቷን አንቆ በመያዝ፤ ሁለተኛ ተከሳሽ ደግሞ በባጃጅ አግቶ በመውሰድ ለ30 ደቂቃ ያክል በጫማ ማሰሪያ ገመድ አሰቃይተው እንደገደሏት የመቐለ ከተማ ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።
አንደኛ ተከሳሽ ግድያውን ከፈጸመ በኋላ ወደ ስራ እንደገባ፤ ገድለው ከቀበሯት ከሶስት ቀናት በኋላም አባቷ አቶ ተክላይ ግርማይን 3 ሚሊየን ብር እንደጠየቀው ተገልጿል።
ሁለተኛ ተከሳሽም ከአንደኛ ተከሳሽ እኩል የወንጀሉ ተባባሪ መሆኑን ያስረዳው ዐቃቤ ሕግ ይህ የግድያ ወንጀል ጭካኔ የተሞላበት በመሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ማስረጃ የመረመረው ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች የፈጸሙት የወንጀል ድርጊት ጭካኔ የተሞላበት መሆኑን በማረጋገጥ የፍርድ ውሳኔ ሰጥቷል።
በዚህም ታዳጊዋ ላይ የግድያ ወንጀል የፈፀመው 1ኛ ተከሳሽ በሞት፣ 2ኛ ተከሳሾች ደግሞ በዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አሳልፏል።