Fana: At a Speed of Life!

የቀድሞ የትግራይ ክልል ታጣቂዎች ችግሮችን በውይይት በመፍታት በጋራ መስራት እንደሚገባ አስገነዘቡ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞ የትግራይ ክልል ታጣቂዎች ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት በመፍታት ለሀገር ዕድገት በትብብር መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በመቐለ የተሀድሶ ስልጠና ማዕከል የገቡ 320 የቀድሞ ታጣቂዎች ስልጠናቸውን በማጠናቀቅ የዘላቂ ማቋቋሚያ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደየመጡበት አካባቢ ተመልሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም በዕዳጋ-ሀሙስ እና መቐለ የተሀድሶ ስልጠና ማዕከላት 640 የትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች ስልጠናቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ።

ሰልጣኞቹ ስልጠናውን ወስደው ወደማህበረሰቡ ሲመለሱ የልማትና የሰላም አካል የሚሆኑበትን ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ገልጸው በስልጠናው መሰረት በሚደረግላቸው የገንዘብ ድጋፍ በግልም ሆነ በማኅበር በመደራጀት የተሻለ የልማት ስኬት ለማስመዝገብ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአንድ አንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የሰላም ችግሮችንም በሰላማዊ ውይይት መፍትሔ በመስጠት ለሀገር ዕድገት በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በቀጣይም አቅማቸው በፈቀደው ሁሉ የሀገር የልማት አካል በመሆን ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሰሩ ማረጋገጣቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

በብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን የፕሮግራም ዕቅድና ክትትል ዳይሬክተር ኮሎኔል በላይ አበበ÷የቀድሞ የትግራይ ክልል ታጣቂዎች በየአካባቢያቸው ከሄዱ በኋላም በዘላቂነት ለማቋቋም ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የቀድሞ ታጣቂዎች በሚደረግላቸው ድጋፍ የሀገርና የክልሉ የልማትና የሰላም አካል እንዲሆኑ የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን በቀዳሚነት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.