የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራር የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራር የነበሩት ጃል ሰኚ ነጋሳ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ።
ጃል ሰኚ ነጋሳ መንግሥት ያቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ነው ከአቶ ሽመልስ አብዲሳ ጋር የሰላም ስምምነቱን የፈረሙት፡፡
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት÷ የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ለመጡት ምስጋና አቅርበዋል።
ከጦረኞች በላይ ጦርነትን የሚያባብሱት ስለጦርነት የማያውቁ ናቸው ያሉት ፊልድ ማርሻሉ÷ እኔ ካለኝ ልምድ አንፃር ጦርነት ጎጂ በመሆኑ የሰላምን መንገድ መርጣችሁ በመምጣታችሁ ልትመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
ይህ አይነቱ ተግባር በሌሎች አካባቢዎችም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ መግለጻቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡
አቶ ሽመልስ በበኩላቸው የኦሮሞ ሕዝብ በባህሉ መሰረት ሰላም ይውረድ ብሎ ያቀረበውን ጥሪ ተቀብላችሁ በመምጣታችሁ በክልሉ መንግሥት ስም አመሠግናለሁ ብለዋል።
የመከላከያ ሠራዊቱ ለሰላም ስምምነቱ ላበረከተው አስተዋፅኦም አቶ ሽመልስ አመሥግነዋል፡፡
በዚህ ዓለም የሰው ልጅ የፖለቲካ ልዩነት ያለው መሆኑን ያወሱት ጃል ሰኚ ነጋሳ÷ እኛም ያለንን የፖለቲካ ልዩነት በጠመንጃ ከመፍታት በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ወስነን ነው ስምምነቱን የመረጥነው ብለዋል።
ስምምነቱ ለኦሮሞ ሕዝብ ትልቅ እፎይታን እንደሚሰጥም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡