አሜሪካ ለታይዋን የ385 ሚሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ሽያጭ ውል አጸደቀች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ለታይዋን የ385 ሚሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ሽያጭ ውል ማጽደቋን አስታውቃለች፡፡
የጦር መሳሪያ ሽያጩ የኤፍ-16 ተዋጊ ጄት መለዋወጫ እቃ፣ የራዳር ሥርዓትና የወታደራዊ መገናኛ ግብዓቶችን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡
የአሜሪካ መከላከያ ደህንነት ትብብር ኤጀንሲ እንደገለጸው÷ የጦር መሳሪያው ከቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ጀምሮ ለታይዋን ተደራሽ ይሆናል፡፡
የጦር መሳሪያው የታይዋንን አየር ሃይል ለማጠናከርና የቀጣናውን ሃይል ሚዛን ለማስጠበቅ እንደሚያስችል ተመላክቷል፡፡
የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ÷ዋሺንግተን ለታይዋን ያጸደቀችውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ውል አድንቀዋል፡፡
የታይዋንና አሜሪካ ወታደራዊ ትብብር ተጠናክሮ እንደቀሚቀጥል ማረጋገጣቸውንም ዘዲፌንስ ፖስት ዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል ቻይና የግዛቴ አንድ አካል የምታላት ታይዋን ከአሜሪካ ጋር የምታደርገው ግንኙነት ሉዓላዊነቷን የሚጥስ ቀይ መስመር እንደሆነ በተደጋጋሚ ትገልጻለች፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ቻይና በታይዋን ላይ መጠነሰፊ ወታደራዊ ጫና እያሳደረች እንደምትገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
አሜሪካና ታይዋን በዚህ ድርጊታቸው የሚቀጥሉ ከሆነም ቤጂንግ ወታደራዊ እርምጃ እንደምትወስድ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቋ ይታወሳል፡፡