የሲቲው አማካይ ሮድሪ ከተገመተው ጊዜ ቀድሞ ወደ ሜዳ ሊመለስ እንደሚችል ፍንጭ ሰጠ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የማንቼስተር ሲቲው የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ሮድሪ ከተገመተው ጊዜ ቀደም ብሎ ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ሜዳ ሊመለስ እንደሚችል ተናግሯል፡፡
ተጫዋቹ ባለፈው መስከረም ወር ሲቲና አርሴናል 2 አቻ በተለያዩበት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በቀኝ ጉልበቱ ላይ ባጋጠመው ጉዳት የውድድር ዓመቱ እስከሚጠናቀቅ ከሜዳ እንደሚርቅ ሲነገር ቆይቷል፡፡
ሆኖም ተጫዋቹ “የእኔ እቅድ የውድድር ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት በሚቀጥሉት ስድስት ወይም ሰባት ወራት ወደ ሜዳ መመለስ ነው፤ ካሰብኩት በላይ በጣም የተሻለ እየሰራሁ ነው” ብሏል፡፡
ተጫዋቹ ከተጎዳ በኋላ ማንቼስተር ሲቲ ያደረጋቸውን 6 ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም፤ በተለይ በፕሪሚየር ሊጉ በሜዳው በቶተንሃም ሆትስፐር 4 ለ 0 የተሸነፈበት ውጤት እጅግ አስደንጋጭ ነበር፡፡
ከትናንት በስቲያ በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ፌይኖርድን 3 ለ 0 ሲመራ ቢቆይም በመጨረሻ 3 አቻ የተለያየበት ውጤትም ብዙዎችን አስገርሟል፡፡
ውጤቱን ተከትሎም አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ በራሳቸው ላይ አካላዊ ጉዳት ማድረሳቸው ይታወቃል፤ በውጤት ማጣቱ ምክንያትም ጫና ውስጥ መግባታቸውም ተሰምቷል፡፡