ህጻን ልጅን በመጥለፍ 10 ሚሊየን ብር በመጠየቅ የተከሰሱ በጽኑ እስራት ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ህጻን ልጅን በመጥለፍ ከወላጆቹን 10 ሚሊየን ብር እንዲከፈላቸው ሲጠይቁ በፀጥታ አካላት ክትትል የተያዙት ግለሰቦች በጽኑ እስራት እንዲቀጡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የልዩ ልዩ ከባድ ወንጀል ችሎት ውሳኔ ሰጠ።
የፍትህ ሚኒስቴር የህጻናትና ሴቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ መሪጌታ ሚስጥሩ ይግዛው፣ ዘውዲቱ ገብሬ እና ብሩክ ቸኮል የተባሉ ተከሳሾች ላይ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና አንቀጽ 590 ንዑስ ቁጥር 1 ለ እንዲሁም ንዑስ ቁጥር 2 (ሠ) ስር የተመላከተውን ድንጋጌ መተላለፋቸውን ጠቅሶ በህዳር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ለአካለ መጠን ያልደረሰ ህጻንን መጥለፍ ወንጀል ክስ ማቅረቡ ይታወሳል።
በዚህ ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ፤ ተከሳሾች ህጻን ለመጥለፍ እና ብር ለመቀበል አስቀድመው ባደረጉት የስምምነት መነሻ መሰረት 2ኛ ተከሳሽ ዘውዲቱ ገብሬ ቀደም ብላ በቤት ሰራተኛነት ተቀጥራ ስትሰራበት በነበረበት ቤት ውስጥ እድሜው 2 ዓመት ከ11 ወር የሆነው ህጻን መኖሩን ለአንደኛ ተከሳሽ በሰጠችው ጥቆማ መሰረት ከህጻኑ ቤተሰቦች ብር ለመቀበል በመነጋገርና በመስማማት 2ኛ ተከሳሽ ስራዋን ለቃ ከቆየችበት የመኖሪያ ቤት በድጋሚ ተቀጥራ እንድትገባ መደረጉ ተዘርዝሯል፡፡
በስምምነታቸው መሰረት ጥቅምት 6 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ ለሚኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው አያት ጣዕም ዳቦ ቤት እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ከሚገኘው በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ ከምትሰራበት የመኖሪያ ቤት ውስጥ ህጻን ሳሙኤልን ማስቲካ ልግዛለት ብላ በማታለል ይዛው ከቤት በመውጣት በወቅቱ እዛው አካባቢ ይጠብቁዋት ከነበሩ 1ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ጋር በመገናኘት ከአዲስ አበባ ውጭ ህጻኑን ጠልፈው መሰወራቸው በክሱ ተመላክቷል።
በዚህ መልኩ ከተሰወሩ በኋላ 1ኛ ተከሳሽ ለህጻኑ አባት ስልክ በመደወል ህጻኑ ከእነሱ ጋር እንዳለ እና 10 ሚሊየን ብር ካላመጡ እንደሚሸጡት በመግለጽና በማስፈራራት ሲደራደር በአ/አ ፖሊስ፣ በፌዴራል ፖሊስ እና በአማራ ክልል ፖሊስ እንዲሁም በደህንነት መስርያ ቤት ከፍተኛ ኦፕሬሽን ስራ በጥቅምት 16 ቀን 2015 ዓ.ም 1ኛ ተከሳሽ በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ውስጥ መያዙ የተጠቀሰ ሲሆን፣ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ኤጀሬ ወረዳ አዲስ ዓለም ከተማ ጨረቃ ሠፈር በሚገኘው 1ኛ ተከሳሽ ተከራይቶት በነበረው ቤት ውስጥ እጅ ከፍንጅ ሊያዙ መቻላቸው በክሱ ተገልጿል።
በዚህ መልኩ የቀረበባቸው ክስ ዝርዝር ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን በመስጠታቸው፤ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ ምስክሮችን አቅርቦ ቃል አሰምቷል
ፍርድ ቤቱም የምስክሮችን ቃል መርምሮ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ በሰጠው ብይን ተከሳሾቹ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን ማስተባበል ባለመቻላቸው በተከሰሱበት ድንጋጌ ስር ጥፋተኛ ብሏቸዋል።
ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ ወንጀሉ በስምምነት የተፈጸመ መሆኑን ጠቅሶ፤ የቅጣት ማክበጃ እና ማቅለያ አስተያየት በመያዝ በዛሬው ዕለት የቅጣት ውሳኔ ሰጥቷል።
በዚህም 1ኛ ተከሳሽ መሪጌታ ሚስጥሩ ይግዛው በ7 ዓመት፣ 2ኛተከሳሽ ዘውዲቱ ገብሬ በ6 ዓመት ከ6 ወራት እንዲሁም 3ኛ ተከሳሽ ብሩክ ቸኮል በ5 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል።
በታሪክ አዱኛ