ፕሬዚዳንት ፑቲን አዲሱ የኦርሺኒክ ሚሳኤል ጥቅም ላይ እንደሚውል ገለፁ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬን በሀገራቸው ላይ ለምትሰነዝረው ጥቃት አፀፋ ለመስጠት አዲሱ የኦርሺኒክ ሚሳኤል ጥቅም ላይ እንደሚውል ገለፁ፡፡
ፕሬዚዳንቱ ይህን የገለፁት የዩክሬንን ትንኮሳ ተክትሎ ዲፕማሲያዊ ድጋፍ ለማግኘት በወዳጅ ሀገራቸው ካዛኪስታን ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ነው፡
በአስታና ባደረጉት ንግግር የሩሲያ ጦር በአዲሱ ኦርሺኒክ ሚሳኤል ጥቃት ለመፈፀም የዩክሬን ኢላማዎችን እየለየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሞስኮ ቀደም ሲል በርካታ የኦርሺኒክ ሚሳኤሎችን ታጥቃ ነበር ያሉት ፕሬዚዳንት ፑቲን÷ በቅርቡ ተሞክሮ ውጤታማ የሆነው ይህ የመካከለኛ ርቀት ሚሳኤል በብዛት እየተመረተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የመጀምሪያው የኦርሺኒክ ሚሳኤል ዩክሬን የምዕራባውያንን የረጅም ርቀት ሚሳኤሎች በመጠቅም ለፈፀመችው ጥቃት አፀፋ ለመስጠት ጥቅም ላይ መዋሉንም አስታውሰዋል፡፡
ኦርሺኒክ አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚስተካከለው የሚሳኤል አይነት የለም ያሉት ፑቲን÷ ሚሳኤሉ ከመሬት በታች የተቀበሩ ጠንካራ ኢላማዎችን ሳይቀር በተሳካ ሁኔታ ማጥቃት እንደሚችል መግለጻቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡
ከድምፅ በአስር እጥፍ እንደሚፈጥን የተነገረው የኦርሺኒክ ሚሳኤል በውስጡ በርካታ አረር ተሸካሚ ጥይቶች ያሉት ሲሆን የተመረጠለትን ኢላማ በደቂቃዎች ውስጥ ወደ ፍርስራሽነት የመቀየር አቅም አለው ተብሏል፡፡