ከ263 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የሕክምና መሳሪያዎች ተሰራጭተዋል- ዶ/ር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ263 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የሕክምና መሳሪያዎች መሰራጨታቸውን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡
6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ በስብሰባው የምክር ቤቱ አባላት ላቀረቡት ጥያቄዎችና አስተያየቶች በሰጡት ማብራሪያ÷ የወባ ስርጭቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጨምሮ እንደሚታይ ጥናቶች እንደሚያሳዩ ገልጸው በኢትዮጵያ የወባ ስርጭት ተጋላጭትን የሚጨምሩ 222 ወረዳዎች እንደተለዩ አንስተዋል፡፡
በዓለምም ሆነ በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ መቀያየር የወባ ተጋላጭነትን ቁጥር መጨመሩንም ጠቁመው ከአጋርና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የላቦራቶሪ አቅም ተገንብቶ በዘርፉ ምርምር እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የመከላከል ስራ ላይ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እስከ ታች ድረስ በመውረድ የቅኝት ስራ ቀደም ተብሎ መካሄዱንም ጠቁመዋል፡፡
በ2017 ሩብ ዓመት ብቻ ከ8 ሚሊየን በላይ የጸረ ወባ መድሐኒቶች ለህሙማን የማድረስ ስራ መሰራቱንና የጤና ኤክስቴንሽ አገልግሎት የሚሰጡ ኬላዎችም ወደ 140 ከፍ ማለታቸውን ተናግረዋል፡፡
በጤና ተቋማት ሚሰጠውን አገልግሎት ለማጥራት እየለየን ነው ያሉት ሚኒስትሯ÷በተለይ ግጭት የነበረባቸው አካባቢዎች ላይ 251 የሚሆኑ የጤና ተቋማትን የማዘጋጀትና የማስፋፋት ስራ እንዲሁም አዳዲስ አቅሞችን ለመገንባት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በሩብ ዓመቱ ከ263 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የህክምና መሳሪያዎች መሰራጨታቸውን የገለፁት ሚኒስትሯ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነ አልትራሳውንድ ገጣጣሚ ተቋም እየተገነባ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በየሻምበል ምህረት