ሕግን በማያከብሩ የነዳጅ ኩባንያዎች ላይ ጠንካራ ርምጃ ይወሰዳል – ሚኒስቴሩ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የተቀመጠውን ሕግና ሥርዓት አክብርው በማይሰሩ የነዳጅ ኩባንያዎች ላይ ጠንከር ያለ ርምጃ እንደሚወሰድ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) አሳሰቡ፡፡
የነዳጅ ምርቶች አቅርቦት፣ ስርጭት እና ግብይት ላይ በሚስተዋሉ ክፍተቶች ዙሪያ ከነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
በዘርፉ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከልም÷ የነዳጅ ህገ ወጥ ግብይት፣ በበርሜል እና በጀሪካን የሚደረጉ ሽያጮች፣ ነዳጅ ማደያ ውስጥ እያለ የለም ብሎ መለጠፍ እና በህገ ወጥ መንገድ ሌሊት መሸጥ የሚሉት እንደሚገኙበት አብራርተዋል፡፡
ለተጠቀሱት ችግሮችም በቀዳሚነት ኃላፊነት የሚወስዱት የነዳጅ ኩባንያዎች መሆናቸውን በአፅንኦት ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የተቀመተውን ሕግና ሥርዓት አክብርው በማይሰሩ ኩባንያዎች ላይ ጠንከር ያለ ርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡