Fana: At a Speed of Life!

 ጓርዲዮላን ምን ነካቸው?

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ስፔናዊው የእግር ኳስ ሊቅ አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ከትናንቱ ጨዋታ በኋላ ጭንቅላታቸውን እና አፍንጫቸውን በጥፍራቸው መቦጫጨራቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

በውድድር ዓመቱ ማንቼስተር ሲቲ እያሳየ ባለው ደካማ እንቅስቃሴ ምክንያት ከተጫዋቹ ጋር እሰጣገባ ውስጥ የገቡት አሰልጣኙ÷ በተከታታይ ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ የሥነ ልቦና ጫና ውስጥ መግባታቸው እየተነገረ ነው፡፡

በተለይም ቶተንሃም ሆትስፐር በኢትሃድ 4 ለ 0 ከረታቸው በኋላ መልበሻ ክፍል ውስጥ ለተጫዋቾቻቸው ስሜት ያመዘነበት ንግግር ሲያደርጉ ተደምጠዋል፡፡

ከኢቲሃዱ ሽንፈት በአግባቡ ያላገገሙት አሰልጣኙ÷ ትናንት ምሽት በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ክለባቸው ፌይኖርድን 3 ለ 0 ሲመራ ቢቆይም በተከታታይ በተቆጠሩበት ጎሎች 3 አቻ ተለያይቷል፡፡

በውጤቱ በተከፉ የውኃ ሰማያዊዮቹ ደጋፊዎች የተተቹት ጓርዲዮላ÷ ከጨዋታው በኋላ አስተያየት በሚሰጡበት ወቅት ጭንቅላታቸውን እና አፍንጫቸውን በጥፍራቸው ቦጫጭረው መታየታቸው እያነጋገረ ነው፡፡

በወቅቱም ጋዜጠኛው የአካል ክፍላቸውን ለምን በጥፍራቸው እንደቦጫጨሩ ሲጠይቃቸው÷ “ራሴን መጉዳት ፈልጌ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ተንታኞች እንደሚሉትም “ጓርዲዮላ ያጋጠማቸውን ተደጋጋሚ ሽንፈት ተከትሎ እየደረሰባቸው ባለው የደጋፊዎች ትችት ምክንያት የሥነ-ልቦና ጫና ውስጥ ገብተዋል፡፡”

በቅርቡ በማንቼስተር ሲቲ ቤት ለመቆየት የሁለት ዓመት ተጨማሪ ኮንትራት የፈረሙት አሰልጣኙ÷ በውድድር ዓመቱ በፕሪሚየር ሊግ፣ ኤፍ ኤ ካፕ እና ሻምፒየንስ ሊግ ባደረጓቸው ጨዋታዎች አራቱን ሲሸነፉ አንዱን አቻ ተለያይተዋል፡፡

በፕሪሚየር ሊጉ በቶተንሃም ሆስትስፐር ያጋጠማቸው ሽንፈት ከ52 ጨዋታዎች በሜዳ ያለመሽነፍ ጉዞ በኋላ የአሰልጣኙ አስከፊው ሽንፈት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

አሰልጠኝ ፔፕ ጓርዲዮላ በባርሴሎና፣ ባየርን ሙኒክ እና ማንቼስተር ሲቲ በአሰልጣኝነት ባገለገሉባቸው ዓመታት በሁሉም ውድድሮች 38 ዋንጫዎችን አንስተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.