Fana: At a Speed of Life!

የእስራኤልና ሂዝቦላህ የተኩስ አቁም ስምምነት መተግበር ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤልና ሂዝቦላህ በትናትናው ዕለት ባደረጉት የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት ዛሬ መተግበር መጀመሩ ተሰምቷል፡፡

የእስራኤል የጸጥታ ካቢኔ ትናንት ባደረገው ምክክር የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንዲደረስ መወሰኑ ይታወቃል፡፡

የእስራኤልና ሂዝቦላህ ጦርነት ማብቂያ ስምምነት በዛሬው ዕለት መሬት ይዟል ሲል የዘገበው ቢቢሲ፥ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ዘላቂ ይሆናል ወይ የሚለው አሳሳቢ ጥያቄ መሆኑም እየተነሳ መሆኑን ጠቅሷል፡፡

ሆኖም በሁለቱ አካላት የተደረሰው ስምምነት ቀላል የሚባል እንዳልሆነና ለሰላም አንድ እርምጃ የሚያቀርብ እንደሆነም ነው እየተገለጸ የሚገኘው፡፡

በተኩስ አቁም ስምምነቱ መሰረት የእስራኤል ጦር በ60 ቀናት ውስጥ ከሊባኖስ ለቆ የሚወጣ ሲሆን፥ የሊባኖስ ጦር ኃይሎች በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል በተኩስ አቁም ስምምነቱ መሰረት ለመስፈር ዝግጅት ጀምሯል።

ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችም የእስራኤል ጦር ለቆ እስኪወጣ ድረስ ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

በተኩስ አቁም ስምምነቱ መሰረት የሊባኖስ ጦር 5 ሺህ ወታደሮችን እንደሚያሰፍርም ተጠቁሟል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.