የዲጂታል ኢትዮጵያ ትራንስፎርሜሽን የጋራ ርብርብ እንደሚጠይቅ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮምና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በአጋርነት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማዘመን ባበለጸጉት የኢኮሜርስ ዲጂታል ግብይት ፕላትፎርም ዙሪያ ከአምራች ኢንዱስትሪ ተወካዮችና ባላድርሻ አካላት ጋር ተወያዩ፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ÷ ፕላትፎርሙ ዘርፉን የሚቀይር መሆኑን በመግለጽ ለአምራች ኢንዱስትሪው ገበያን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ፣ ከግብአት አቅራቢዎች ያላቸውን ትስስርና የምርት አቅርቦት ሰንሰለትን አስተማማኝ ለማድረግ እንዲሁም በመረጃ የተመሰረተ ውሳኔ ለመስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡
አክለውም የዘርፉ መዘመን ለኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ ይህም አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ በመገንባት የዜጎችን ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባሻገር ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን እንደሚጨመር አብራርተዋል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በበኩላቸው ÷ የዲጂታል ኢትዮጵያ ትራንስፎርሜሽን የጋራ ርብርብ እንደሚጠይቅ በመግለጽ የዚሁ አካል የሆነውን ዲጂታል የግብይት ፕላትፎርም ተግባራዊ ለማድረግ ኩባንያቸው አስቻይ የመሰረተ ልማት አቅም የዘረጋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ዘርፉን በቴክኖሎጂ ከማስታጠቅ ባሻገር ክህሎት በማሳደግ፣ ፖሊሲና መመሪያዎችን በማሻሻል ምቹ ስነ-ምህዳር በመፍጠር ኢትዮጵያን በፍጥነት ከሸማችነት ወደ አምራችነት ማሸጋገር እንደሚቻል አክለዋል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተወካዮች ÷ፕላትፎርሙ የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪ ምርቶችን ተወዳዳሪነት በማሻሻል ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሂደት በመተካት ዘርፉን ለማነቃቃት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ያላቸውን እምነት መግለፃቸውን የኢትዮ -ቴሌኮም መረጃ ያመላክታል፡፡