ኢትዮጵያ የአፍሪካ የቡና ምርት ተወዳዳሪ እንዲሆን የበኩሏን ሚና እንደምትወጣ አስታወቀች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ የቡና ምርት ከማሳ እስከ ገበያ ተወዳዳሪና ለችግሮች የማይበገር ዘርፍ እንዲሆን የበኩሏን ሚና እንደምትወጣ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለፁ።
የበይነ_አፍሪካ የቡና ድርጅት ከፍተኛ የፖሊሲ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በመድረኩ ፥ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ብቻ ሳትሆን ምርታማነትና የምርት ጥራትን በመጨመር የዓለም የገበያ መሪ መሆንን ትሻለች ያሉ ሲሆን ለዚህም ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን የሚቋቋም የቡና ምርታማነት ለማረጋገጥ እየሰራች ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት 5 ዓመታት በቢሊየን የሚቆጠሩ የቡና ችግኞችን መትከሏን ገልፀው ፥ የወጪ ንግድ ገቢዋም መጨመሩን አብራርተዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ውጪ ከሚላክ የቡና ገቢ ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ማቀዷን ያነሱት ሚኒስትሩ ፥ የምርት ጥራት፣ ገበያ ተደራሽነትና ተጠቃሚነት ላይ አበክራ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ከጥሬ ቡና ይልቅ እሴት በመጨመር ዘርፉ የሚያመነጨውን ዕድል ለመጠቀም ስለማቀዷም አብራርተዋል።
የአፍሪካ የቡና ዘርፍ የሚገጥሙትን ችግሮች በዘላቂነት መፍትሔ እንዲያገኝም ከሀገራት ጋር በትብብር እንደምትሰራ ማረጋገጣቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ከማሳ እስከ ዓለም ገበያ ባለው የቡና እሴት ሰንሰለት ከፖሊሲ ትግበራ ጀምሮ አስፈላጊውን ስራ በማከናወን ዘርፉ ተወዳዳሪና ለችግሮች የማይበገር ሆኖ እንዲቀጥል በትብብር መስራት እንደሚያሻም ተናግረዋል።
ከአምራችነት እስከ ቡና ላኪዎች ተጠቃሚነትን በማጎልበትና የገበያ መዳረሻን ማስፋት እንደሚገባም ገልፀው ፥ ኢትዮጵያ የበይነ-አፍሪካ ቡና ድርጅት ግቦች እንዲሳኩም የመሪነት ሚናዋን እንደምታወጣ አረጋግጠዋል።