ትራምፕ በቻይና፣ ሜክሲኮና ካናዳ ላይ አዲስ ታሪፍ እንደሚጥሉ አስታወቁ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ዶናልድ ትራምፕ ወደ ፕሬዚዳንትነት ስልጣናቸው ዳግም በሚመለሱበት ጥቂት ቀናት ውስጥ በቻይና፣ ሜክሲኮና ካናዳ ላይ አዲስ ታሪፍ እንደሚጥሉ ጠቁመዋል፡፡
47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ ስራ ሲጀምሩ የሚጥሉት አዲስ ታሪፍ ወደ አሜሪካ የሚደረግ ህገወጥ ስደትና የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውርን ለመግታት በማሰብ እንደሆነም ተነግሯል።
በመጪው ጥር በዓለ ሲመታቸው ከተካሄደ በኋላ ወዲያውኑ ከሜክሲኮ እና ካናዳ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ የሚጥል አስፈፃሚ ትዕዛዝ ይፈርማሉ ተብሏል።
በተመሳሳይም በቻይና ላይ ተጨማሪ 10 በመቶ ታሪፍ እንደሚጣል የተገለጸ ሲሆን፤ እነዚህ ውሳኔዎች ከአሜሪካ ሦስት ታላላቅ የንግድ አጋሮች ጋር ያለው ውጥረትን እንደሚያባብስም ተሰግቷል፡፡
በአሜሪካ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ የትራምፕ ሀሳብ በተጨባጭ ካለው እውነት ጋር እንደሚጋጭ መግለጹን ቢቢሲ ዘግቧል።
ቻይና ከአሜሪካ ጋር ያላት የኢኮኖሚ እና የንግድ ትብብር የጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ነው ብላ እንደምታምን የገለጹት የኤምባሲው ቃል አቀባይ፥ ማንም በንግድና በታሪፍ ጦርነት አያሸንፍም ብለዋል፡፡
በአሜሪካና ቻይና መካከል ለዓመታት የከረረ የንግድ ውዝግብ ቢፈጠርም ዋሽንግተን አሁንም 15 በመቶ የቤጂንግን ምርት ወደሀገሯ ታስገባለች፡፡