በሶማሊያ ሊከሰት በሚችለው ማንኛውም ቀውስ የፌዴራሉ መንግስት ሀላፊነት የሚወስድ መሆኑ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሊያ ሊከሰት በሚችለው ማንኛውም ቀውስ የፌዴራሉ መንግስት ሀላፊነቱን የሚወስድ መሆኑን የጁባላንድ ግዛት መንግስት አስታወቀ።
የጁባላንድ መንግስት በሶማሊያ ቀውስ ለመፍጠር የሀገሪቱ የፌዴራል መንግስት ያልተገባ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን በመግለጽ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም የሶማሊያ ህዝብና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሀገሪቱን ፌዴራል መንግስት ቀውስ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስገንዝቧል።
ሀገሪቱን ወደ ከፋ ቀውስ ለመክተት በሚደረገው እንቅስቃሴ የፌዴራሉ መንግስት እጅ እንዳለበት አመላክቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሀገሪቱን የፌዴራል ስርዓት በመጣስ የሀገሪቱ መንግስት ህገወጥ የሆነ ጣልቃ ገብነትን እየተከተለ እንደሆነ የገለጸው የጁባላንድ ግዛት መንግስት፤ ፖለቲካዊ አለመረጋጋትን በመፍጠር የጁባላንድን ሰላምና መረጋጋት የሚያውክ ድርጊት በፌዴራሉ መንግስት እየተፈጸመ መሆኑን አንስቷል።
ፌዴራል መንግስቱ በጌዶ ክልል ያጋጠመውን ውድቀት ተከትሎ ከህግ ውጪ በራስ ኮምቦኒ ወታደሮችን እንዳሰፈረ ያነሳው መግለጫው፤ ይህ ወታደራዊ ሃይል ከጁባላንድ የጸጥታ ሃይሎች በተቃራኒ መቆሙን ገልጿል።
ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባትም የጁባላንድ መንግስት ግልጽነት ለመፍጠር ጉዳዩን በስፋት አብራርቷል።
ከህግ ውጪ በራስ ኮምቦኒ የሰፈረው ጎሳን መሰረት ያደረገ የሚሊሻ ሃይል ህጋዊና ህገ-መንግስታዊ ሂደትን ያልተከተለ መሆኑን ጠቅሶ፤ የጁባላንድ መንግስት በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ሰላም ማስከበር ተልዕኮ (አትሚስ) ፋንታ ጎሳን መሰረት ያደረገ የሚሊሻ ሃይል በራስ ኮምቦኒ እንዲሰፍር የማይፈቅድ መሆኑን አረጋግጧል።
ከዚህ ቀደም አትሚስ ለቋቸው የነበሩት ቡርጋዮ፣ ኩዳ፣ አብዳላ ቢሮሌ፣ ኤልዋክ እና የኪስማዮ አካባቢዎች በጁባላንድ የጸጥታ ሃይሎች መያዛቸውን አስታውቋል።
የፌዴራሉ መንግስት ተጨማሪ ሃይል እንዲያሰማራ የጁባላንድ መንግስት ያቀረበው ምንም አይነት ጥያቄ ባለመኖሩ ከያዙት ቦታ ለቀው እንዲወጡ የጠየቀው የጁባላንድ መንግስት፤ ድርጊቱ ቀውስ የሚፈጥር በመሆኑ በጽኑ እንደሚያወግዘው ገልጿል።
በመሆኑም የፌዴራሉ መንግስት ከድርጊቱ በመቆጠብ ችግሩ እንዳይባባስ መስራት እንዳለበት አመልክቶ፤ በሶማሊያ ሊከሰት በሚችለው ማንኛውም ቀውስ የፌዴራሉ መንግስት ሀላፊነቱን የሚወስድ መሆኑን ህዝቡና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲገነዘብ የጁባላንድ መንግስት በመግለጫው አመልክቷል።
ፑንትላንድ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐሙድ የሥልጣን ጊዜያቸውን ለማራዘም የህገ-መንግስት ማሻሻያ ማድረጋቸውን እንደማትቀበል ማስታወቋ ይታወሳል፡፡
የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ ተከትሎ በፈረንጆቹ 1998 ራስገዠነቷን ያወጀችው ፑንትላንድ ከሌሎች ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ በቀጥታ ውይይት ማድረግና ግንኙነት መመስረት እንደምትችል ገልፃለች፡፡