የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አምራቾችን የማምረት አቅም 40 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው በጀት ዓመት የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አምራቾችን የማምረት አቅም 40 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት በናይጄሪያ ሌጎስ በተካሄደው የ2024 ዓለም አቀፍ የጤና አቅርቦት ሰንሰለት ውድድር በምርጥ ኬዝ አቅራቢነት ተሸላሚ ሆኗል።
ይህንን አስመልክቶ በተዘጋጀ መድረክ የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ፍሬህይወት አበበ እንዳሉት÷ ሚኒስቴሩ መከላከልና አክሞ ማዳን ላይ ያተኮረ የጤና ፖሊሲን እየተከተለ ይገኛል፡፡
ፖሊሲውን ተፈጻሚ ለማድረግ የመድኃኒት አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው÷ የመድኃኒትና ሕክምና ግብዓቶችን በጥራትና በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በመድኃኒት አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር መንግስት ድጎማ እያደረገ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡
ከዚህ ቀደም በጥሬ እቃ አቅርቦት ችግር የሀገር ውስጥ አምራቾች ከአቅማቸው 25 በመቶ ያህሉን ብቻ ሲጠቀሙ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
አሁን ላይ በተሰጠው ትኩረት የሀገር ውስጥ መድሃኒት አምራቾች አቅም 36 በመቶ መድረሱንና በተያዘው ዓመት 40 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሚኒስቴሩን የመድኃኒት ግዢ የሚፈፅምና የሚያሰራጭ እንደሆነ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡