Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ቻይና ከሳይበር ደህንነት ጋር በተያያዘ በጋራ ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መከሩ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቸን ሃይ ጋር ሁለቱ ሀገራት ከሳይበር ደህንነት ጋር በተያያዘ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ በዚህ ወቅት÷ ተቋሙ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ያለማቸውን ምርት እና አገልግሎቶችን እንዲሁም በተለያዩ የሳይበር ደህንነት ዘርፎች እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎችን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር በተለያዩ የልማት ዘርፎች ያላትን ትብብር በሳይበር ደህንነት ዘርፍም አጠናክራ መቀጠል እንደምትፈልግ ዋና ዳይሬክተሯ መግለጻቸውን የአስተዳደሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

አምባሳደር ቸን ሃይ በበኩላቸው÷ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የኢትዮጵያን የሳይበር ደህንነት በማረጋገጥ የሀገሪቷን ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ እድገት ከመደገፍ አንፃር እየሰራቸው ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ የልማት ዘርፎች ያላቸውን ጠንካራ ትብብር በሳይበር ደህንነት ዘርፍ በመድገም የተጠናከረ ስራ መስራት እንዳለበቸው ገልፀው÷ ለዚህም ስኬት የበኩላቸውን አስተዋፆ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.