የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍታት ይገባል የሚለውን ጽኑ አቋሟን በተግባር የገለጠ ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍታት ይገባል የሚለውን ጽኑ አቋሟን በተግባር የገለጠ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።
የአፍሪካ አህጉራዊ የሰላም ኮንፈረንስ “የበለፀገችና ሰላማዊ አፍሪካን እንገንባ” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍታት ይገባል የሚል ጽኑ አቋም አላት።
በአፍሪካ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታን እየፈጠረች መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከሰላም ስምምነቱ ባለፈ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ በቀጣናው ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ገንቢ ሚና ተወጥታለች ብለዋል።
ለአፍሪካ ሰላምና ብልፅግና የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ገቢራዊ መሆን ድርሻው የጎላ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፥ ሴቶችና ወጣቶች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያግዛልም ብለዋል።
የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱአለም በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በሰላም ስምምነቱ መሰረት የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታትና ወደ ማህበረሰቡ በመቀላቀል ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ያላትን ቁርጠኝነት አሳይታለች ብለዋል።
በኢትዮጵያ የወል ትርክት ተገንብቶ ህብረ ብሔራዊነት እንዲሰፍን ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው÷የሰሜኑን ጦርነት በሰላም ለመቋጨትና የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እውን እንዲሆን ጥረት መደረጉን አንስተዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ በስምምነቱ መሰረት ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በመልሶ ግንባታና መልሶ ማቋቋም ስራዎች ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው የሽግግር ፍትህ፣ ብሔራዊ ምክክርና የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ለሰላም ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያዎች መሆናቸውን እንደገለጹም ኢዜአ ዘግቧል