አትሌት ሃምሳ አለቃ የወርቅ ውኃ ጌታቸው ለኢትዮጵያ መከላከያ የወርቅ ሜዳሊያ አስገኘች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አትሌት ሃምሳ አለቃ የወርቅ ውኃ ጌታቸው ለኢትዮጵያ መከላከያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች፡፡
በናይጀሪያ አቡጃ ከተማ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 2ኛው የመላው አፍሪካ የጦር ኃይሎች ስፖርት ፌስቲቫል እንደቀጠለ ሲሆን÷ ኢትዮጵያን የወከለው የመቻል ስፖርት ክለብ አትሌቲክስ ቡድን በውድድሩ እየተሳተፈ ነው፡፡
በዚህም በ5 ሺህ ሜትር የሴቶች ፍፃሜ ውድድር አትሌት ሃምሳ አለቃ የወርቅ ውኃ ጌታቸው የወርቅ እንዲሁም አትሌት ሃምሳ አለቃ አያልፍም ዳኛቸው የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
በሌላ በኩል በርዝመት ዝላይ ሴቶች ምክትል አስር አለቃ በፀሎት ዓለማየሁ እና በዲስከስ ውርወራ ሴት አስር አለቃ ዙርጋ ኡስማን የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆን ችለዋል፡፡
እስካሁን ባለው ውድድር የመቻል ስፖርት ክለብ አንድ የወርቅ እና አራት የብር ሜዳሊያዎችን ማግኘቱን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡