ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ለምታደርገው ጥረት ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ለምታደርገው ጥረት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ተወካዮች ገለጹ።
የፌደራል መንግስት እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የአህጉራዊና ዓለማ አቀፋዊ ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት በመቀሌ ከተማ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶና መልሶ የማቋቋም ስልጠና የማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓት ተካሂዷል።
በዝግጅቱ የተገኙት የአፍሪካ ሕብረት ተወካይ ሜጀር ጄኔራል ራዲና ስቴፈን÷ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት ሰላምን ለማጽናት የሚደረገው ጥረት በጥሩ ሁኔታ እየተጓዘ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ ሕብረት አማካኝነት በተለያዩ ጊዚያት የተካሔዱ ስትራቴጂክ የአፈፃጸም የምክክር መድረኮች ላይ የፕሪቶሪያው ስምምነት የሰላም ሂደቱን ለማጽናት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን እንደተመላከተ ገልጸዋል።
የፌደራል መንግስት በብሔራዊ ምክክር ግጭቶችን በእርቅና ይቅርታ በመቋጨት በዘላቂ ሀገራዊ እርቅና ሰላምን ለማምጣት የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።
ለዚህም ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ለምታደርገው ጥረት ዓለም አቀፍ አጋሮችና የአፍሪካ የግል ተቋማት የሚያደርጉትን ድጋፍ ማጠናከር ይገባቸዋል ብለዋል።
በመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ገባይዴ ዶ÷ የትጥቅ ማስፈታትና የመልሶ ማቋቋም የተሀድሶ ስልጠና መጀመሩ የሰላም ስምምነቱ የሰመረ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት በተሀድሶ ስልጠና መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ የሚገኘው ጥረትም የጥይት ድምጽን ከማስቀረት ባሻገር የክልሉን ነዋሪዎች ተስፋ የሚያለመልም መሆኑን ገልጸዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎችም ከተሀድሶ ስልጠናው በኋላ ወደ ማህበረሰቡ ሲመለሱ የሰላምና የልማት ምርታማነት አቅም መሆን እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በምታከናውነው የቀድሞ ታጣቂዎችን የመልሶ ማቋቋም ስራ ድጋፍ ላደረጉ የመንግስታቱ ድርጅት ተቋማት ምስጋና አቅርበው በቀጣይም እገዛውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የአውሮፓ ሕብረት እና ለጋሽ ሀገራት ተወካይ ሶፊ ፍሮም-ኢመስበርገር÷ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት በተሀድሶ ስልጠና መልሶ ለማቋቋም የሚያደርጉት ድጋፎች የኢትዮጵያን ሰላምና ደኅንነት በጽኑ መሰረት ላይ ለማኖር ገንቢ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ትርጉም ያለው እርምጃ እየወሰደች መሆኑን የጠቀሱት ተወካዩ፤ ለዚህም የመንግስታቱ ድርጅት ተቋማትና ለጋሽ አገራት በትብብር እየሰሩ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶ ስልጠና መልሶ በማቋቋም ሰላምና ብልጽግናዋ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በዝግጅቱ የታደሙ የፌደራል መንግስት እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የአህጉራዊና ዓለማ አቀፋዊ ተቋማት ተወካዮችም የቀድሞ ታጣቂዎችን የተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ለመስጠት የተደረጉ የዝግጅት ሂደቶችን የሚያሳየውን ኤግዚቢሽን ጎብኝተዋል።