ኔቶ ሩሲያ አዲስ የፈጸመችው የሚሳኤል ጥቃት ዩክሬንን ከመደገፍ እንደማያስቆመው አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመቸው የባላስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ሀገሪቱን ከመደገፍ እንደማያስቆመው አስታወቀ፡፡
ሩሲያ በትናንትናው እለት ከድምጽ ፍጥነት በአስር እጥፍ የሚልቅ አህጉር አቋራጭ የሃይፐርሶኒክ ባላስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ዩክሬን ላይ መፈጸሟን ተከትሎ ኔቶ ቃል አቀባይ ፋራህ ዳክላላህ እንደገለጹት፤ የሩሲያ የሚሳኤል ጥቃት ኔቶ ለዩክሬን የሚያደርገውን ድጋፍ እንደማያስቆመው አረጋግጠዋል።
ሩሲያ ከአስትራካን ግዛት ያስወነጨፈችው ሚሳኤል በ15 ደቂቃ ውስጥ የዩክሬኗን ድኒፕሮ ከተማን መምታቱን የዩክሬን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለኔስኪ የሩሲያ አዲሱ የሚሳኤል ጥቃት የጦርነቱን መስፋት እንደሚያመላክት ገልጸው፤ አጋሮቻቸው ምላሽ እንዲሰጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ በአስፋላጊ ጉዳዮች ሁሉ ከዩክሬን ጎን መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን ቻይና ሁለቱ ወገኖች ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥሪ አቅርባለች፡፡
የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አዲሱ የሀይፐርሶኒክ ባላስቲክ ሚሳኤል ጥቃት አሜሪካ በግዴለሽነት ለፈጸመችው ስህተት ምላሽ ነው ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡