ፓም ቦንዲ የትራምፕ አስተዳደር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተደርገው ተሾሙ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ 47ኛው ፕሬዚዳንት ተደርገው የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ አንጋፋዋን አቃቢተ ህግ ፓም ቦንዲን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በማድረግ ሹመት ሰጡ፡፡
ትራምፕ ሹመቱን የሰጡት ቀደም ሲል ዕጩ አድርገው የመረጧቸው ማት ጋኤዝ በተነሳባቸው ተቃውሞ ሃላፊነቱን እንደማይቀበሉ ካሳወቁ በኋላ ነው።
ፓም ቦንዲ ረጅም ዓመታትን በህግ አገልግሎት ላይ የሰሩ ሲሆን የፍሎሪዳ ግዛት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በመሆንም አገልግለዋል፡፡
ትራምፕን በአደባባይ በመደገፍ የሚታወቁት ፓም ቦንዲ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በብቃት እንደሚወጡም ተነግሯል።
ዶናልድ ትራምፕ ሹመቱን ከሰጡ በኋላ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ፓም ቦንዲ 20 ዓመታትን የሚጠጋ ልምድ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ፓም ወንጀልን በመከላከል እና የፍሎሪዳ ጎዳናዎችን ሰላማዊ በማድረግ ለሰሩት ስራ አድናቆት ይገባቸዋል ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡