በአማራ ክልል ከ1 ሚሊየን በላይ የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው በጀት ዓመት በአማራ ክልል ከ1 ሚሊየን 233 ሺህ 744 የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ስራ እና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አወቀ ዘመነ እንደገለጹት፤ በክልሉ ሊፈጠር ከታቀደው የስራ ዕድል ውስጥ 80 ከመቶው ቋሚ እና 20 ከመቶው ጊዜያዊ ነው።
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ 141 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን ገልጸዋል።
በክልሉ 6 ሺህ 175 አዲስ ኢንተርፕራይዞችን የማደራጀት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር መያዙን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በክልሉ ከ82 ሺህ በላይ ዜጎች በሁሉም የሙያ ዘርፍ ጤናማ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት እንዲመቻችላቸው እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።
በመንግስት ደረጃ የሚፈጠሩ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪቶች የዜጎች ሁለንተናዊ ደህንነት እንዲጠበቅ ከማድረግ በተጓዳኝ ለሀገርም የሚኖረው ፋይዳ ቀላል አይደለም ሲሉም ነው የገለጹት።
በእሸቱ ወ/ሚካኤል