ፕሬዚዳንት ፑቲን በአሜሪካና ብሪታኒያ ላይ ጥቃት ሊፈፅሙ እንደሚችሉ አስጠነቀቁ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በአሜሪካ እና ብሪታኒያ ላይ ጥቃት ሊፈፅሙ እንደሚችሉ አስጠነቀቁ፡፡
ፕሬዚዳንት ፑቲን ማስጠንቀቂያውን የሰጡት ዩክሬን ከኔቶ አባል ሀገራት እና አሜሪካ በታጠቀቻቸው የረጅም ርቀት ሚሳኤሎች ሩሲያ ላይ ጥቃት መፈፀሟን ተከትሎ ነው፡፡
ጥቃቱን አስመልክቶ ፑቲን በሰጡት መግለጫ ÷ አሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ አርሚ ታክቲካል በተባለው ዘመናዊ ሚሳኤል ሩሲያ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡
ሩሲያ አዲስ የስትራቴጂክ ሚሳኤሎችን በመጠቀም የአፀፋ ምላሽ መስጠቷን እና በአፀፋ ጥቃቱ የሩሲያ ባላስቲክ ሚሳኤል የዩክሬን የጦር መሰረተ ልማቶችን ኢላማ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ለዩክሬን መሳሪያ በመላክ ጥቃት እንዲፈፀም ለሚያደርጉ ሀገራት ሞስኮ ምላሽ የመስጠት መብት አላት ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የሩሲያ ጦር ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ባደረጉት አሜሪካ እና ብሪታኒያ ላይ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
ሞስኮ እንደአስፈላጊነቱ አዳዲስ የሚሳኤል ስርዓቶችን ተግባራዊ ልታደርግ እንደምትችልም አመላክተው፤ ጦርነቱን በንግግር ለመፍታት ሀገራቸው ቁርጠኛ መሆኗን ማረጋገጣቸውን ሲኤንቢሲ ዘግቧል።