የዓለም ባንክ ለጤናው ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ አዲስ ከተሾሙት የዓለም ባንክ ካንትሪ ዳይሬክተር ሚሪያም ሳሊም ጋር ባደረጉት ውይይት በቀጣይ በጤናው ዘርፍ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በትኩረት መክረዋል፡፡
ዶ/ር መቅደስ ዳባ÷ ኢትዮጵያ በኮቪድ ወረርሽኝ ጊዜም ሆነ በግጭት ወቅት የዓለም ባንክ ድጋፍ እንዳልተለያት አስታውሰዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር እና የዓለም ባንክ ትብብር የጤና ዘርፍ አጀንዳን በፍጥነት ወደፊት ለማራመድ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡
ከዓለም ባንክ ጋር በትብብር እየተሰሩ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በጤናው ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን በፍጥነት ለማከናወን ያለውን ዝግጁነት አብራርተዋል፡፡
ሚኒስትሯ በዚህ ረገድ የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል በሚቻልበት ሁኔ ላይም ምክክር የተደረገ ሲሆን÷ የወባ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ከዓለም ባንክ ጋር በቅርበት ለመስራት መግባባት ላይ መደረሱ ተጠቁሟል፡፡
ሚሪያም ሳሊም በበኩላቸው ÷ጤና ሚኒስቴር በተለይም የእናቶች እና ህጻናት ጤናን በማሻሻል ረገድ ያስመዘገበውን ውጤት አድንቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ለሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት እንደሆነች መናገራቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡