Fana: At a Speed of Life!

ለክላስተር ግብርና የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ እመርታ እያሳየ ነው – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ለክላስተር ግብርና የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ እመርታ እያሳየ ይገኛል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ፥ በሰላም ተምሳሌቷና ጎተራዋ ሙሉ በሆነችው ደጀን ወረዳ ባየነው የጤፍ ክላስተር ልማት ተደንቀናል ብለዋል።

ኢትዮጵያን ወደ ከፍታዋ መውሰድ የሚቻለው በግብርና እና በሌሎች የልማት መስኮች የተጀመሩ ሥራዎችን በማጠናከር እንደሆነ አንስተዋል፡፡

ለዚህም እንደሀገር ለክላስተር ግብርና የሰጠነው ትኩረት ከፍተኛ እመርታ እያሳየ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

በአማራ ክልል ትርፍ አምራች ከሆኑ አካባቢዎች አንዱ በሆነው ምስራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ የተመለከቱትን ጤፍ በክላስተር የማልማት ሥራም አድንቀዋል፡፡

በዘንድሮ የመኸር እርሻ ለግብዓት አቅርቦትና ለዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡

ይህን ተከትሎም ከፍተኛ ምርት እንደሚገኝ ተዘዋውረን የተመለከትነው የሰብል ቁመና ያሳያል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ በቀጣይም ለመስኖ ልማትና ለሰላም ትልቅ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን ብለዋል።

ማህበረሰቡም የሰላምና የልማት አርበኝነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የምስራቅ ጎጃም ዞን ሕዝብ በተለይም የደጀን ወረዳና አካባቢዋ ነዋሪዎች ላሳዩት ድንቅ የጤፍ ልማትና ላደረጉላቸው ደማቅ አቀባበልም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.