Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል የመንገድ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ተቋራጮች ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል የተቋረጡ እና የተጓተቱ የመንገድ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለህዝብ አገልግሎት እንዲውሉ ተቋራጮች የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ተጠየቀ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በፈረንጆች 2022 ተጀምሮ በታቀደለት ጊዜ ያልተጠናቀቀውን ከአኩላ አቻኛ 82 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን የመንገድ ስራ ተመልክተዋል።

የመንገዱ ግንባታ እስካሁን 43 በመቶ ብቻ ተከናውኗልም ተብሏል፡፡

ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ እና ልሎች የሥራ ሃላፊዎች ከፕሮጀክቱ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ጋርም ተወያይተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሯ በዚሁ ጊዜ÷ የመንገዱ መጓተት በአካባቢው ባሉ ሕዝቦች የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ላይ እንቅፋት ሆኗል ብለዋል፡፡

የማህበረሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንገዱ በፍጥነት መሰራት እንዳለበት በመግለጽ ተቋራጩ ሀገር በቀል እንደመሆኑ መጠን ለሀገሩ እየሰራ መሆኑን ተረድቶ ያሉበትን ክፍተቶች አርሞ መንገዱን እንዲያጠናቅቅ ጠይቀዋል።

በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተጠናቀው ለህዝብ አገልግሎት እንዲውሉ ተቋራጮች የበኩላቸውን ሀላፊነት እንዲወጡም አሳሰበዋል።

የክልሉ መንግስት የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በታቀደላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለህዝቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል እንደሚሰራም መገለጹን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.